Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የአርባምንጭ ኮንፈረንስ ሪዞርት የከተማዋን ውበት አንድ ርምጃ ከፍ የሚያደርግ ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 27፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የአርባምንጭ ኮንፈረንስ ሪዞርት የከተማዋን ውበትና የቱሪዝም አቅም አንድ ርምጃ ከፍ የሚያደርግ ነው አሉ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዛሬው ዕለት ሪዞርቱን መርቀው በከፈቱበት ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፥ ኢትዮጵያ ውስጥ ድንቅ የተፈጥሮ ፀጋዎች ካሏቸው ክልሎች አንዱ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መሆኑን አንስተዋል፡፡

ክልሉ የብዝሃ ቋንቋ፣ ባህል እንዲሁም የታሪካዊ ቅርሶችና ድንቅ የተፈጥሮ ሀብቶች መገኛ መሆኑን ገልጸው፥ የእግዜር ድልድይ፣ የነጭ ሳር ብሔራዊ ፓርክ እንዲሁም ተራሮችንና አረንጓዴ ስፍራዎችን የያዘችው አርባምንጭ የክልሉ ድንቅ ውበት ማሳያ ናት ብለዋል፡፡

የገበታ ለትውልድ መርሃ ግብር አካል የሆነው የአርባምንጭ ኮንፈረንስ ሪዞርት የግሉ ዘርፍ በትብብር መስራት ከቻለ መሰል ግዙፍ ፕሮጀክቶችን መገንባት እንደሚቻል ያሳየ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

የሪዞርት ግንባታው አርባምንጭ መንግዶችና ሌሎች መሰረተ ልማቶች የተሟሉላት እንዲሁም በቂ የሰው ኃይል ያላት ከተማ መሆኗን በማመላከት የመጣ ውጤት ነው ብለዋል፡፡

ሪዞርቱ አርባ ምንጭ በተፈጥሮ የነበራትን ውበት አንድ ርምጃ ወደፊት ከፍ የሚያደርግ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ የክልሉና የከተማዋ አመራሮች እንዲሁም ማህበረሰቡ በዚህ ስኬት ሳይኩራራ ተጨማሪ ልማቶችን ሊያስቀጥል እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የአርባምንጭ ኮንፈረንስ ሪዞርት ከ1 ሺህ 300 በላይ ሰዎችን የሚያስተናግድ የስብሰባ አዳራሽና በሐይቅ ላይ የተገነባ ልዩ ተንሳፋፊ ሬስቶራንትን ያካተተ ነው፡፡

ሪዞርቱ መንግስት ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በሌሎች አካባቢዎች የኮንፈረንስ ቱሪዝምን በማስፋፋት ኢትዮጵያን የዓለም አቀፍ መድረኮች ማዕከል ለማደረግ እያደረገ ያለውን ጥረት ከማጠናከር ባለፈ ለአካባቢው ማኅበረሰብ ሰፊ የሥራ ዕድል ይፈጥራል፡፡

በሚኪያስ አየለ

Exit mobile version