አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 25፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአዲሱ ስርዓተ-ትምህርት ተማሪዎች 12ኛ ክፍልን ሲጨርሱ የሙያ ባለቤት እንደሚሆኑ ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የትምህርት ሚኒስትሩ ዶክተር ጌታሁን መኩሪያ በአጠቃላይ የትምህርት ዘርፍ ውስጥ የሙያ ትምህርቶችን በሁሉም የሙያ ዘርፎች በመስጠት የተማረ እና በዘርፉ እውቀት ያለው ባለሙያ እንዲፈጠር ትኩረት ሰጥተን እንሰራለን ብለዋል።
ሚኒስትሩ ይህን ያሉት የትምህርት ሚኒስቴር የአጠቃላይ የትምህርት ዘርፉ የ10 ዓመት ዕቅድ ውይይት በሚያካሄድበት ወቅት ነው።
በውይይቱ ላይ አጠቃላይ ትምህርት አንዱ የሙያ መማሪያ ዘርፍ እንዲሆን ትምህርት ሚኒስቴር ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑ ተነግሯል።
ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ላይ ሙያ ያለው ተማሪን ለመፍጠር በቀጣይ የሙያ ትምህርቶች ከመደበኛ ትምህርት ጋር በተጣጣመ መልኩ ጎን ለጎን እንደሚሰጥም ተገልጿል።
በዚህም ተማሪዋች የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ሲያጠናቅቁ የሙያ ባለቤት ይሆናሉ ተብሏል።
ከዚህም በተጨማሪ የጎልማሶችና መደበኛ ያልሆኑ ትምህርቶች በቀጣይ ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የተነሳ ሲሆን፥ ይህን ለማስፈፀም የጎልማሶችና መደበኛ ያልሆነ የትምህርት
ዘርፍ ተቋቁሟል።
እውቀትን ወደ ታች በማውረድ ለሁሉም ተደራሽ እንዲሆን ማድረግ የ10 ዓመቱ አንዱ
የዕቅድ አካል መሆኑንም በውይይቱ ላይ መነሳቱን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

