Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ ልዑካን ቡድን አባላት በላሊበላ አረንጓዴ ዐሻራቸውን አኖሩ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 27፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ተቀማጭነታቸውን በአዲስ አበባ ያደረጉ የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ ልዑካን ቡድን አባላት በታሪካዊቷ ላሊበላ ከተማ የአረንጓዴ ዐሻራ ችግኝ ተከላ መርሐ ግብር አካሂደዋል።

የሀገራት አምባሳደሮችና የዓለም አቀፍ ተቋማት መሪዎች፣ በዩኔስኮ በተመዘገበው የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ቅጥር ግቢ ነው አረንጓዴ ዐሻራቸውን ያኖሩት።

በታሪካዊቷ የላሊበላ ጉብኝት በማድረግ ላይ የሚገኘው የዲፕሎማቲክ ልዑካን አባላት በትላንትናው ዕለት የዓለም ድንቅ ቅርስ የሆነውን የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን ጎብኝተዋል።

ከጉብኝታቸው በተጓዳኝም በዛሬው ዕለት በቅርስ መዳረሻው የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ቅጥር ግቢ ውስጥ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር አካሂደዋል።

የልዑካኑ የችግኝ ተከላ የኢትዮጵያን የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ከቅርስና አካባቢ ጥበቃ ጋር በአርዓያነት ተሰናስሎ የሚሰራበት ዓለም አቀፋዊ የልማት አጀንዳ መሆኑ ተገልጿል።

ጉብኝቱና የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብሩ የኢትዮጵያን ጥንታዊነት፣ አስደናቂ የኪነ-ሕንጻ ጥበብና የባህል ዕሴቶችን ለዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ይበልጥ ለማስተዋወቅ ትልቅ አጋጣሚን ፈጥሯል።

ጉብኝቱ ኢትዮጵያ ለቱሪስቶች አስተማማኝና ማራኪ መዳረሻ መሆኗን ለዓለም በመገለጥ የቱሪዝም ዘርፍ ለማነቃቃት ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር ተመላክቷል።

የዓለም አቀፍ ማሕበረሰብ ተወካዮች በቅርስ ስፍራው ችግኝ መትከላቸው የዓለም ቅርሶችን የመንከባከብና የአየር ንብረት ለውጥን በጋራ የመከላከል ዓለም አቀፋዊ ትብብር ማሳያ ተደርጎ እንደሚወሰድም ኢዜአ ዘግቧል፡፡

Exit mobile version