Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

165 ኢትዮጵያውያን ከሊባኖስ ተመለሱ

አዲስ አበባ፣ ነሀሴ 25፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በሊባኖስ በአሰሪዎች በደልና የመብት ጥሰቶች፣ የአካልና የስነ-ልቦና ጉዳት የደረሰባቸው እንዲሁም መጠለያና ምግብ ያጡ የነበሩ 165 ኢትዮጵያውያን ወደ ኢትዮጵያ ተመለሱ።

ሊባኖስ የሚገኘው ቆንስላ ጄኔራል ጽህፈት ቤት ከኢትዮጵያ ኮሙኒቲ ማህበር እና ከሌሎች ድጋፍ ከሚያደርጉ በጎ አድራጎት ድርጅቶችን ግለሰቦች ጋር በመተባበር የጉዞ ሰነዶቻቸውንና ሌሎች ጉዳዮችን በመጨረስ ትናንት ማታ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለሱ ተደርጓል ተብሏል።

በሊባኖስ የኢትዮጵያ ኮሙኒቲ ማህበር በመጠለያ፣ በህክምና፣ በኮሮናቫይስ ምርመራዎች፣ አልባሳት፣ ምግብና መጠጦች፣ ማስኮች፣ ሳኒታይዘሮችን እንዲያገኙ በማድረግ በኩል ጉልህ አስተዋጽኦ ማድረጉን ቆንስላ ጄኔራል ጽህፈት ቤቱ አስታውቋል፡፡

በተጨማሪም ቤተክርስቲያናት፣ በጎ አድራጎት ድርጅቶች፣ ማህበራት፣ ቡድኖችና ግለሰቦችም ድጋፍ አድርገዋል ነው የተባለው፡፡

በሊባኖስ በአሰሪዎች በደልና የመብት ጥሰቶች፣ የአካልና የስነ-ልቦና ጉዳት የደረሰባቸው እንዲሁም መጠለያና ምግብ ያጡ የነበሩ 165 ዜጎችን ኮሙኒቲ ማህበሩንና ሌሎች አካላት የአውሮፕላን ቲኬቶችን ወጪዎችን በመሸፈንና እና ሌሎችም እገዛዎችን በማድረግ ዜጎች ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ላደረጉት ትብብር ቆንስላ ጽህፈት ቤቱ ምስጋናውን አቅርቧል፡፡

157 ዜጎች አሁን በኢትዮጵያ ኮሙኒቲ ማህበር መጠለያ ውስጥ ሲገኙ እነዚህ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገር ቤት እንዲመለሱ ቆንስላ ጄኔራል ጽህፈት ቤቱ የጉዞ ሰነዳቸውን እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን ለማስጨረስ እየሰራ ይገኛል።

የእነዚህንም ዜጎች የትራንስፖርት ቲኬት እና ሌሎች ተያያዥ ወጪዎች ተሸፍኖላቸው በቶሎ ወደ ሀገራቸው መመለስ ይችሉ ዘንድ ይህ የተጀመረው ትብብር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ተጠይቋል።

በሌላ በኩል 75 ኢትዮጵያውያን በ8ኛ ዙር የትራንስፖርት ወጪያቸውን በራሳቸው በመሸፈን ወደ አገር ቤት ለመጓዝ ተመዝግበው የነበሩ የመኖሪያ ፍቃድ ያልነበራቸው ዜጎቻችን የጉዞ ሰነድና የመውጫ ቪዛ የተሰራላቸው እንዲሁም ምርመራ ያጠናቀቁ ሲሆን ቲኬቶቻቸውን ራሳቸው በመግዛት ዛሬ ማታ ወደ ኢትዮጵያ ይመለሳሉ፡፡

በተመሳሳይ 155 ኢትዮጵያውያንም በዚህ ሳምንት ወደ ሀገራቸው እንደሚመለሱ ሊባኖስ ከሚገኘው ቆንስላ ጄኔራል ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

Exit mobile version