Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ለሀዋሳ ሐይቅ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት ከ1 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር በላይ ተሰበሰበ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 22፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በተገኙበት የሀዋሳ ሐይቅ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት ሀገር አቀፍ የገቢ ማሰባሰቢያና የምስጋና መርሐ ግብር ዛሬ ተካሂዷል፡፡

በመድረኩም ለሀዋሳ ሐይቅ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት የቀረበውን የድጋፍ ጥሪ ተከትሎ ከተቋማትና ከክልሉ ባለሃብቶች ከ1 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡ ተገልጿል፡፡

የሀዋሳ ሐይቅ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት የፍቅር ሐይቅ፣ የአሞራ ገደል እና የአሳ ገበያን ተፈጥሯዊ ጸጋቸውን በማልማት ወደ ላቀ ዘመናዊነት እንዲሸጋገሩ ለማስቻል ያለመ ነው፡፡

የሀዋሳ ሐይቅ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት የሀዋሳ ከተማን ገጽታ በመቀየር ለቱሪዝም ዘርፉ እድገት ከፍተኛ ፋይዳ እንደሚኖረው ተመላክቷል፡፡

ሀዋሳ ከተማን ተመራጭ የቱሪዝም መዳረሻ ከማድረግ ባለፈ የከተማዋንና የማሕበረሰቡን ኢኮኖሚ ከማሳደግ አንጻር ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወትም ተጠቁሟል፡፡

በመርሐ ግብሩ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህን ጨምሮ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ፣ የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) እና የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ ጥራቱ በየነ ተገኝተዋል፡፡

በዙፋን አምባቸው

Exit mobile version