Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ከአጀንዳ ማሰባሰብ እስከ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 28፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአንድ ሀገር የፖለቲካ ዕጣ ፈንታ የሚወሰነው በጋራ መግባባት እና በአንድነት በሚቀረጹ የጋራ አቅጣጫዎች ነው። ኢትዮጵያ የጀመረችው የሀገራዊ ምክክር ሂደት፣ የሕዝብን ድምፅ ከመሰብሰብ ወደ ተጨባጭ የፖሊሲ እና የሀገራዊ መግባባት ምክረ-ሃሳቦች የሚሸጋገርበት ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ደርሷል።

በብዙዎች ዘንድ የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደቱን ከሀገራዊ ምክክር ጉባኤው ጋር ያለውን ልዩነት ባለመረዳት ሂደቶቹን አንድ አድርገው ይወስዷቸዋል። ነገር ግን ሁለቱ ሂደቶች ያላቸው መተጋገዝ እንደተጠበቀ ሆኖ በዓላማ፣ በተሳታፊዎች እና በሚሰጡት ውጤት ረገድ ልዩነት አላቸው።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አጀንዳዎችን ከሕዝብ የማሰባሰብ፣ የመለየት እና የመቅረጽ ሥራውን አጠናቅቆ ወደ ወሳኙ የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ምዕራፍ መሸጋገሩ ይታወቃል።

በዚህም በምክክር ጉባኤው የሚመከርባቸውን ስምንት አጀንዳዎች በሰኔ 17 ቀን 2018 ዓ.ም ይፋ አድርጓል።

አጀንዳዎቹ በንዑስ ርዕሶች የተከፋፈሉ ቢሆኑን ዋናዋና አጀንዳዎቹ የሀገር ግንባታ፣ የመንግሥት አደረጃጀትና ቅርፅ፣ የፌዴራል ከተሞች ሁኔታ፣ የሐይማኖት ጉዳይ፣ የተቋማት ግንባታና የህግ የበላይነት፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያ ተጠቃሚነት በአርሶ አደሩና በአርብቶ አደሩ ላይ፣ ሙስናና መልካም አስተዳደር እንዲሁም የሰላም ጉዳይ ናቸው።

እነዚህን ዋና ዋና አጀንዳዎች ለመለየት ባለፉት ዓመታት የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አካታችና ሁሉን አቀፍ ሂደት ተከትሏል።

ይህ ሂደት ለኢትዮጵያ የፖለቲካ ምህዳር ታሪካዊ ፋይዳ ነበረው። በዚህ ምዕራፍ ባለድርሻ አካላት እንደ ሀገር አለመግባባትን ሲያስከትሉ የነበሩ መሰረታዊ ጉዳዮችን ለይተው አቅርበዋል፣ የሕዝቡ ሕመሞች፣ ሥጋቶች፣ ምኞቶች እና ተስፋዎች በአጀንዳ መልክ ተሰባስበዋል።

በተጨማሪም ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር ሲባል በየአካባቢው ቅርበት ባላቸው ቦታዎች ውይይቶች ተካሂደው ለምክክር ጉባኤው የተለዩትን አጀንዳዎች ለመቅረጽ የሚሆን ግብዓት ተገኝቷል፤ ለሀገራዊ ምክክር ጉባኤው ጥሬ ሀሳቦችን አቅርቧል።

አሁን የአጀንዳ ማሰባሰብ ምዕራፉ ተዘግቶ የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ሊካሄድ ዋዜማው ላይ ደርሷል።

የሀገራዊ ምክክር ጉባኤው ከአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደቱ ጋር ፍጹም የተለያየ ነው። ሁለቱ ጉዳዮች በዓላማ፣ በአቀራረብ እና በተሳታፊዎቹ አወቃቀር ይለያያሉ።

የቀድሞው ሂደት አጀንዳዎችን “ከማሰባሰብ” ጋር የተያያዘ ነበር። ጉባኤው ግን በተሰባሰቡ እና በተቀረጹ አጀንዳዎች ላይ ተመስርቶ “መግባባት” ላይ የሚደረስበት ነው። ጉባኤው የሃሳብ ነፃነት እና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ማዕከል በማድረግ፣ በአጀንዳዎቹ ላይ የጋራ መግባባት በመፍጠር ምክረ ሃሳቦች ይቀረጹበታል።

አጀንዳ የማሰባሰብ ሂደቱ ሰፊ ሕዝባዊ ውይይቶችን በማካተት የተካሄደ ነው። የምክክር ጉባኤው ግን በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ተሳታፊዎች የተመረጡ ተወካዮችን በማሳተፍ ይካሄዳል። ይህም ውይይቱን ይበልጥ የተጠና እና ወደ ፍጻሜ የሚያደርስ ያደርገዋል።

በአዲስ አበባ ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ የሚካሄደው የምክክር ጉባኤ ከ4 ሺህ በላይ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ወኪሎች በአንድ ማዕከል ተገናኝተው የሀገርን ዕጣ ፈንታ የሚወስኑበት ትልቅ መድረክ ነው።

የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደቱ የሕዝቡን ድምፅ የመስማት እና የመመዝገብ ሥራ ነበር፤ የሀገራዊ ምክክር ጉባኤው ግን የሕዝብ ድምፅ ወደ ተጨባጭ የፖሊሲ እና የሀገራዊ መግባባት ለመተርጎም ምክረ ሃሳቦች ያቀርባል።

Exit mobile version