አዲስ አበባ፣ ሰኔ 28፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ/ር) በምርጫው ድምጽ የሰጠንን ህዝባችንን ተጠቃሚ ለማድረግ አመራሩ እስከ ታች ወርዶ መስራት አለበት አሉ።
የክልሉ የ90 ቀናት ዕቅድ አፈጻጸምን በተመለከተ የመንግሥት የስራ ኃላፊዎች በደሴ ከተማ ተወያይተዋል።
አብዱ ሁሴን (ዶ/ር) በመድረኩ እንዳሉት፤ በሚቀጥሉት 90 ቀናት በተቀመጠው ዕቅድ መሰረት የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ወደ ስራ መገባት አለበት።
የክረምት ስራዎችን ጨምሮ በዋና ዋና የትኩረት ነጥቦች ላይ በትኩረት መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በዋናነት በምርጫው ድምጽ የሰጠንን ህዝባችንን በላቀ ሁኔታ ተጠቃሚ ለማድረግ አመራሩ ዝግጁ ሆኖ እስከ ታች ወርዶ መስራት አለበት ብለዋል።
የመንግሥትን አፈጻጸም በሁሉም ዘርፍ ማሳደግ፣ የኑሮ ውድነቱን መቀነስና የዜጎችን ገቢ ማሻሻል እንዲሁም በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ ይገባል ነው ያሉት።
የክልሉን ሰላም ለማረጋገጥ የተሰሩ ተግባራት ውጤታማ እንደነበሩ አስታውሰው፤ ይህንን በማጠናከር ሰላሙን ወደ አስተማማኝ መንገድ ማምጣት ይገባል ብለዋል።
እቅዱን በተሻለ ሁኔታ ለመፈጸም አመራሩ በቁርጠኝነት ከማህበረሰቡ ጋር በመቀናጀት መስራት እንዳለበትም አመልክተዋል።
በሙሉቀን አበበ

