አዲስ አበባ፣ ሰኔ 28፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ችግሮችን በመተጋገዝ የማለፍ ባህላችንን አጠናክረን መቀጠል አለብን አሉ።
ከንቲባዋ በአዲስ አበባ ከተማ 30ኛው የተስፋ ብርሃን የምገባ ማዕከል በለሚ ኩራ ክ/ከተማ በይፋ መርቀው አገልግሎት አስጀምረዋል።
በምረቃው ወቅት ከንቲባዋ ባስተላለፉት መልዕክት፤ የምገባ ማዕከላቱ መቋቋም ለዜጎቻችን ያለንን ክብርና ፍቅር መግለጫ ነው ብለዋል።
በመዲናዋ ሰው ተኮር ስራዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውን ጠቅሰው፤ ይህም መንግሥት ለዜጎች ተጠቃሚነት የሰጠውን ትኩረት የሚያሳይ እንደሆነ ተናግረዋል።
30ኛው የተስፋ ብርሃን የምገባ ማዕከል የልማት ተነሺና ቋሚ ገቢ የሌላቸውን አቅመ ደካማ የማህበረሰብ ክፍሎችን ለመደገፍ ያለመ መሆኑን ጠቁመው፤ በምገባ ማዕከሉ ግንባታ ሂደት ሚና የነበራቸውን ባለድርሻዎች አመስግነዋል።
በከተማዋ የምገባ ማዕከላትን ከማቋቋም ባለፈ ለዜጎች ቋሚ የስራ ዕድል ለመፍጠር በትኩረት እየተሰራ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ለማህበራዊ ችግር የተጋለጡ ዜጎች በቋሚነት የሚጠቀሙበት ይህ የምገባ ማዕከል በለሚ ኩራ ክ/ከተማ የተከፈተ 4ኛው ማዕከል ነው።
በጀማል አህመድ

