Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የባህር በር፣ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም መከበር

ኢትዮጵያ 130 ሚሊየን ሕዝብ ይዛ ከዓለም አንደኛዋ ወደብ አልባ ሀገር ናት።

የባህር በር ማጣት ለኢኮኖሚዋ፣ ለብሔራዊ ደህንነቷ እና ለጂኦፖለቲካዊ ተፅዕኖዋ ትልቅ ማነቆ ሆኖ ቆይቷል።

ስለሆነም ለኢትዮጵያ የባህር በር ማግኘት፣ የሕልውና እና የብሔራዊ ጥቅምን የማስከበር ቀዳሚ ጉዳይ ነው።

የባህር በር ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነት ወሳኝ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ለወጪና ገቢ ንግድ በዋናነት የምትጠቀመው የጅቡቲን ወደብ ነው።

ለዚህም በየዓመቱ በቢሊዮን የሚቆጠር የአሜሪካ ዶላር ለወደብ ኪራይና ለአገልግሎት ትከፍላለች።

የራስ የወደብ አማራጭ ማግኘት ይህንን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ወጪ ያስቀራል።

የወደብ ባለቤት መሆን የዕቃዎች ዝውውር ፍጥነትን ይጨምራል።

በተጨማሪም የትራንስፖርት እና የሎጂስቲክስ ወጪን በመቀነስ የኢትዮጵያ ምርቶች በዓለም ገበያ ላይ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ያደርጋል።

የባህር በር የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትን ከማስከበር ባሻገር ለብሔራዊ ደህንነትም ዋስትና ነው፡፡

በሌሎች ሀገራት ወደቦች ላይ ብቻ መንጠልጠል፣ በእነዚያ ሀገራት ውስጥ አለመረጋጋት ወይም የፖለቲካ አለመግባባት ሲፈጠር የኢትዮጵያን ደህንነት አደጋ ላይ ይጥላል።

የራስ የባህር በር እንደ ነዳጅ፣ መድኃኒት እና ማዳበሪያ ያሉ ስትራቴጂካዊ ዕቃዎች ያለ ምንም መስተጓጎል እንዲገቡ ዋስትና በመሆን የአቅርቦት ስጋትን ያስወግዳል፡፡

የባህር በር መኖር ጠንካራ እና ዘመናዊ የባህር ኃይል በመገንባት የንግድ መርከቦችን ደህንነት ለመጠበቅ እና የሀገርን ዳር ድንበር ይበልጥ ለማስከበር ያስችላል።

የባህር በር የጂኦፖለቲካዊ ተፅዕኖ እና የመደራደር አቅምንም ይጨምራል፡፡

የቀይ ባህር እና የኤደን ባህረ ሰላጤ ቀጣና ለዓለም ንግድ ቁልፍ መስመር ነው።

ኢትዮጵያ በዚህ መስመር ላይ ቀጥተኛ የባህር በር ሲኖራት በቀጣናው የፖለቲካ እና የደህንነት ውሳኔዎች ላይ ያላት ተፅዕኖ እና የመደራደር አቅም በከፍተኛ ደረጃ ያድጋል።

ወደብ አልባ መሆን በአህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ መድረኮች ላይ ያለንን የፖለቲካ ክብደት ይቀንሰዋል።

የባህር በር ባለቤትነት ግን የኢትዮጵያን የዲፕሎማሲያዊ የበላይነት ከፍ በማድረግ ዓለም አቀፍ ተደማጭነታችን እንዲጨምር ያደርጋል፡፡

ኢትዮጵያ በባህር በርም ሆነ በማንኛውም ጉዳይ ጥቅሞቿን ለማስከበር በጋራ ልማት፣ በሰላማዊ ትብብር እና በዲፕሎማሲ ውይይቶች ታምናለች፡፡

ሰጥቶ በመቀበል መርህ አብራ ማደግን ትሻለች፡፡ ኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄዋን በሰላማዊ መንገድ፣ በዲፕሎማሲ እና በጋራ የመልማት ፍላጎት እንዲሳካ ትፈልጋለች።

የተዘጉ የንግድ በሮች መከፈት ለሀገሪቱ አዳዲስ የኢንዱስትሪ እና የኢንቨስትመንት ዕድሎችን በመፍጠር የወጣቶችን የሥራ አጥነት ችግር ለመቅረፍ ትልቅ አስተዋፅኦ ይኖረዋል።

የባህር በር ማግኘት ለኢትዮጵያ የቅንጦት ጥያቄ ሳይሆን የ130 ሚሊዮን ሕዝብ የወደፊት ዕጣ ፈንታ የሚወሰንበት አንጋፋ ብሔራዊ ጥቅም ነው።

ይህንን ለማሳካት ሰላማዊ የዲፕሎማሲ ጥረቶችን እያጠናከረች ትገኛለች፡፡

ከጎረቤት ሀገራት ጋር በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ ስምምነት እንዲኖር ኢትዮጵያ የዘወትር ተግባሯን ትቀጥላለች፡፡

Exit mobile version