አዲስ አበባ፣ ሰኔ 29፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአውሮፓ ህብረት በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው ሀገራዊ ምክክር ዘላቂ ሰላምና ብሔራዊ አንድነትን ለመፍጠር የሚያስችል ታሪካዊ ዕድል ነው አለ።
በኢትዮጵያ የአውሮፓ ህብረት ልዑክ መሪ አምባሳደር ሶፊ ፍሮም-ኤመስበርገር እንዳሉት ፥ ሀገራዊ ምክክሩ ኢትዮጵያ ዋና ዋና የልዩነት ምንጮችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የምታደርገውን ጥረት የሚያግዝ ወሳኝ ምዕራፍ ነው።
መድረኩ ከተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች የተወጣጡ ዜጎች ሀሳብ የሚለዋወጡበትና የኢትዮጵያን የወደፊት እጣ ፈንታ የሚወስኑ ምክረ-ሃሳቦች የሚያመነጩበት መሆኑን ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ተናግረዋል፡፡
የብሔራዊ ምክክር ኮሚሽኑን አመራር ያደነቁት አምባሳደሯ ፥ የአውሮፓ ህብረት ለምክክሩ ሒደት ሙሉ ድጋፍ እንዳለው አረጋግጠዋል።
ከሀገራዊ ምክክሩ ባለፈ የአውሮፓ ህብረትና የኢትዮጵያ አጋርነት በአየር ንብረት ለውጥ፣ በታዳሽ ኃይል እና በዘላቂ ልማት ላይ ተጠናክሮ መቀጠሉን አመልክተዋል።
በቅርቡ በአዲስ አበባ በሚገኙ ዲፕሎማቶች የተካሄደውን የአረንጓዴ ዐሻራ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ያነሱት አምባሳደሯ ፥ አረንጓዴ ዐሻራና ታዳሽ ኃይል ከነዳጅ የሚለቀቁ በካይ ጋዞችን ለመቀነስ ያላቸውን ጠቀሜታ አብራርተዋል።
በተጨማሪም የአውሮፓ ህብረትና ኢትዮጵያ ግብርናን ለማዘመን እና በሌሎች ዘርፎች ላይ ያላቸውን ትብብር ይበልጥ ለማጠናከር እንደሚሰሩ ጠቅሰዋል፡፡
በሶስና አለማየሁ

