አዲስ አበባ፣ ሰኔ 29፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጥንታዊ የሰው ዘር መገኛ የሆነችው ኢትዮጵያ የበርካታ ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶች ባለቤት ናት፡፡
ቀደም ሲል ከቱሪዝሙ ዘርፍ በላቀ ደረጃ ተጠቃሚ ለመሆን የነበራት እድል ሰፊ ቢሆንም፤ ዘርፉ ከተሰጠው ያነሰ ትኩረት አንጻር ያለውን መልካም እድል እና አቅም ሳትጠቀም ቀርታለች፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ቱሪዝም የኢትዮጵያ የእድገትና ብልጽግና ዋነኛ ምሰሶ ሆኖ በትኩረት እየተሰራባቸው ከሚገኙ ዘርፎች ዋነኛው ሆኗል፡፡
ትኩረት ከተደረገባቸው ጉዳዮችም በዋነኛነት የቱሪዝም አቅም ያላቸው መዳረሻዎችን ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ማሳደግ፣ መሰረተ ልማትን ማሟላትና ገጽታቸውን ዘላቂነት ባለው መልኩ ማስዋብ ቀዳሚዎቹ ናቸው፡፡
ከርዕሰ መዲናዋ አዲስ አበባ በ532 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምስራቅ ባሌ ዞን የሚገኘው ሶፍ ኡመር ዋሻ አስደናቂ የተፈጥሮ መስህብ ስፍራ ነው፡፡
ይህ ስፍራ ስያሜውን ያገኘው ከ1 ሺህ ዓመት በፊት በዋሻው ውስጥ ይኖሩና በውስጡም ሃይማኖታዊ ትምህርት ያስተምሩ ከነበሩት አባት ሼክ ሶፍ ዑመር እንደሆነ ይነገራል፡፡
ውብ በሆኑ ፀጋዎች የተከበበው ይህ የቱሪዝም መዳረሻ ከባሕር ጠለል እስከ 1 ሺህ 385 ሜትር ከፍታ ላይ የሚገኝ መሆኑና ከጫፍ እስከ ጫፍ መንገዱን አቋርጦ ለመጨረስ ከሁለት እስከ ሶስት ሰዓት መፍጀቱ ሥፍራውን እጅግ አስደናቂ ያደርገዋል፡፡
ሌላኛው ዋሻውን አስደናቂ የሚያረገው ውበት ደግሞ የዌብ ወንዝ ሲሆን ነው፤ ከባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ በመነሳት ከመቶ ኪሎ ሜትር በላይ በመጓዝ፤ በዋሻው ውስጥ የሚያቋርጥበት ትዕይንት ለሥፍራው ተጨማሪ ድባብ ፈጥሮለታል፡፡
በዋሻው የሚያቋርጠው ይህ ወንዝ በጉዞው ላይ ሰባት ጊዜ የሚተጣጠፍ ሲሆን÷ ዋሻውን የሚያቋርጥ ማንኛውም ጎብኚ ወንዙን ሰባት ጊዜ እንዲሻገር ያስገድደዋል ፡፡
ይህን አስደናቂ የቱሪስት መዳረሻ ለመጎብኘት ብዙዎች በየዓመቱ ከዓለም ዙሪያ ይተማሉ፡፡እንዲህ ባለ ሁኔታ ብዙዎች ሊያዩት የሚጓጉለት ስፍራ ታድያ አመቺ የሆነ ደረጃውን የጠበቀ መሰረተ ልማት ስላልተሟላለት ለቱሪዝም ዘረፉ የአቅሙ ያክል ሳያበረክት ዘመናትን ተሻግሯል፡፡
አሁን ግን ችግሩን በዘላቂነት የሚፈታ፤ ጎብኚዎች እንደልብ ከውበቱ እንዲቋደሱ ዕድል የሚፈጥር ብሎም አስደናቂው የሶፍ ዑመር ዋሻ እንደ ድንቅ መዳረሻነቱ ለሀገር የሚጠቅበትን ማበርከት እንዲችል የማልማት ሥራ እየተካሄደ ይገኛል።
የበጀት ምንጩ ደግሞ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተፃፈው የመደመር ትውልድ መጽሐፍ ሽያጭ ገቢ ነው። በስፍራው በግንባታ ላይ ያለው የዲንሾ ሎጅ እና በመጠናቀቅ ላይ የሚገኘው የሶፍ ዑመር ሎጅ የቱሪዝም ፕሮጀክትም ለዘርፉ ትልቅ መነቃቃትን የሚፈጥር ሆኗል።
ይህን ውብ ዋሻ ይበልጥ ቀልብ እንዲሰብ እና በተለያዩ የመገናኛ አውታሮች መነጋገሪያ እንዲሆን የሚያስችል ሁነት በያዝነው ዓመት ጥቅምት ወር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) እና ሌሎች አመራሮች በተገኙበት የተካሄደው “የሶፍ ዑመር ወግ” የተሰኘ ውይይት ነው፡፡
ይህ አዲስ መልክ በተለያዩ የመገናኛ አውታሮች ላይ ለዕይታ ከበቃ በኋላ ስፍራውን የሚጎበኙ ሰዎች ቁጥር መጨመሩ መረጃዎች አመልክተዋል፡፡
ሶፍ ዑመር ዋሻን ተመራጭ ኢትዮጵያን በአፍሪካም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ቀዳሚ የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ በሚደረገው ጉዞ ውስጥ የታየው ትጋትና ውጤት ዘርፉን ይበልጥ ለማሳደግ ለሌሎች ሥራዎችም ተምሳሌት የሚሆን ነው፡፡
በመልካም ፈቃዱ

