አዲስ አበባ፣ ሰኔ 29፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የ2018 ትምህርት ዘመን 12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና በተለያዩ ዙሮች በስኬት እየተካሄደ ይገኛል አለ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት።
አገልግሎቱ የ2018 ትምህርት ዘመን የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና በሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች በተለያዩ ዙሮች በስኬት እየተካሄደ መሆኑን ነው ያስታወቀው፡፡
ፈተናው በበይነ መረብ መሰጠት መጀመሩን እና ተፈታኞች በ6 ዙሮች ተከፋፍለው በተሳካ ሁኔታ ፈተናቸውን እየወሰዱ እንደሚገኙ አመልክቷል፡፡
የተወሰኑ የመሠረተ ልማት ተደራሽነትና የኮምፒውተር እጥረት ባለባቸው አካባቢዎች ፈተናውን በአራት ዙሮች በወረቀት ለመስጠት አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል ነው ያለው፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞ በትግራይ ክልል በበይነ መረብ ለመፈተን ለተመዘገቡ 14 ሺህ 755 ተፈታኞች በ6ቱ ዙር ከሰኔ 23 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ፈተናው እየተሰጠ እንደሚገኝ ጠቁሟል።
በሌላ በኩል በወረቀት ለመፈተን ለተመዘገቡ 15 ሺህ 325 የክልሉ ተፈታኞች ፈተናው ከሐምሌ 22 እስከ 24 ቀን 2018 ዓ.ም በመቐለ እና በአክሱም ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ እንደሚሰጥ የአገልግሎቱ መረጃ ያመላክታል።
እነዚህ በወረቀት የሚፈተኑ ተማሪዎች ሐምሌ 20 ቀን 2018 ዓ.ም ወደ መቐለ እና አክሱም ዩኒቨርሲቲዎች በመግባት፣ ሐምሌ 21 ቀን 2018 ዓ.ም የሚሰጠውን ገለጻ በመከታተል ፈተናቸውን መውሰድ እንደሚችሉ ነው የተገለጸው፡፡

