አዲስ አበባ፣ ሰኔ 29፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአውሮፓ የተከሰተውን ከፍተኛ መጠን ያለው ሙቀት ተከትሎ የተቀሰቀሰው ሰደድ እሳት ወደተለያዩ ሀገራት እየተዛመተ ይገኛል፡፡
እስካሁን በስፔን፣ ፖርቹጋል፣ ፈረንሳይ እና ግሪክ በአጠቃላይ 190 ስኩዌር ኪ.ሜ የሚሸፍን ቦታ በእሳት መያያዙ የተገለጸ ሲሆን፥ የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች ሰደድ እሳቱን ለማጥፋት ከፍተኛ ርብርብ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡
በተለይም በደቡባዊ አውሮፓ በተከሰተው የሰደድ እሳት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች አካባቢያቸውን ለቅቀው መሸሻቸውን ዩሮ ኒውስ ዘግቧል፡፡
በአህጉሪቱ ከፍተኛ መጠን ባለው ሙቀት እየተፈተኑ በሚገኙ ሀገራት ቀደም ሲል የተመዘገበው 40 ዲግሪ ሴልሺየስ የሙቀት መጠን ዝቅ አለማለቱ ነው የተገለጸው፡፡
የግሪክ ባለስልጣናት ከሰደድ እሳቱ የሚወጣው ጢስ ለጤና ጠንቅ በመሆኑ ሰዎች በቤት ውስጥ እንዲቆዩ አሳስበዋል፡፡
የአውሮፓ ኅብረት ሰደድ እሳቱን ለማስቆም የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ የእሳት ማጥፊያ ሄሊኮፕተሮችን ማሰማራቱን አስታውቋል፡፡
በትዕግስት ግዛቸው

