አዲስ አበባ፣ ሰኔ 30፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀይማኖቶች የሰላም እንጂ የግጭት ምክንያት ሆነው አያውቁም አሉ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 30ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ተገኝተው ለምክር ቤቱ አባላት ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ እየሰጡ ይገኛሉ፡፡
በኢትዮጵያ ውስጥ ሀይማኖታዊ ግጭቶች እንዳሉ ተደርገው የሚቀርቡ መረጃዎች የተሳሳቱ መሆናቸውን ገልጸው፥ ኢትዮጵያ ውስጥ የሀይማኖት ተቋማት ታሪክ የትብብርና አብሮ የመስራት መሆኑን አውስተዋል፡፡
የአብዛኛው ግጭቶቸ ታሪክ የብሔር፣ የርዕዮተ ዓለም፣ የኢኮኖሚና የኃይል የበላይነት እንዲሁም የግዛት ማስፋፋት መሆኑን አስታውሰው፥ በኢትዮጵያ እነዚህን ፍላጎቶች በሀይማኖት ሽፋን ለማስፈፀም ሙከራዎች መኖራቸውን አንስተዋል፡፡
እምነቶች የሰላም እንጂ የግጭት ምክንያቶች አይደሉም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ኢትዮጵያ ሙስሊሞች ገንዘብ አዋጥተው ቤተክርሰቲያን የሚሰሩበትና ክርስቲያኖች ገንዘብ አዋጥተው መስጊድ የሚሰሩባት ሀገር መሆኗን አውስተዋል፡፡
ይሁን እንጂ ሽፍቶች ለእኩይ ዓላማቸው የሀይማኖት ግጭት ሲፈጥሩ ጀሌዎቻቸው ደግሞ ግጭቱን በማራገብ ለማባባስ ይሞክራሉ ነው ያሉት፡፡
ለምሳሌ በቅርቡ አርሲ የተከሰው ሽፍቶች ጥቃት በመፈፀም እኩይ ተልዕኳቸውን ለማሳካት ሙከራ ባደረጉበት ወቅት ከፀጥታ አካላት ጋር የተፈጠረ ግጭት እንጂ የሀይማኖት ግጭት እንዳልነበረ አብራርተዋል፡፡
በግጭቱ ከሞቱ 11 ሰዎች ውስጥ ስምንት የሚሆኑት የፀጥታ አካላት መሆናቸውን ጠቅሰው፥ ነገር ግን ክስተቱ ሀይማኖታዊ እንደሆንና በአካባቢው ያሉ ክርስቲያኖች እንደተጠቁ ተደርጎ የተወሰደው መረጃ ሀሰተኛ ነው ብለዋል፡፡
የተራገበው ሀሰተኛ መረጃ ምርጫውን ለማደናቀፍ በተለያዩ አካባቢዎች የተደረጉ ሴራዎች አካል መሆኑን ጠቅሰው፥ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ 22 ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው እየተጣራ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
በግጭቱ የተፈናቀሉ ዜጎችም ወደ አካባቢያቸው ተመልሰዋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ አዲስ አበባ ተቀምጠው ሀሰተኛ መረጃ የሚያሰራጩ ግለሰቦች ግን ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ አሳስበዋል፡፡
በሚኪያስ አየለ

