አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 1፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) “በጎነት ለኢትዮጵያ ከፍታ” በሚል መሪ ቃል 5ኛው ዙር ሀገር አቀፍ የወሰን ተሻጋሪ የወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት መርሃ ግብር በዛሬው ዕለት በሀዋሳ ከተማ በይፋ ተጀምሯል።
በመርሃ ግብሩ ማስጀመሪያ ላይ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞን ጨምሮ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች እና ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የተውጣጡ ወጣቶች ተገኝተዋል።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) በወቅቱ እንዳሉት፤ በጎነት ከንፁህ ህሊና የሚመነጭ መልካም አገልግሎት ነው፡፡
ባለፉት አራት ሀገር አቀፍ የወሰን ተሻጋሪ የወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች የተውጣጡ ወጣቶችን በማሳተፍ አመርቂ ተግባራት መከናወናቸውን አስታውሰዋል።
በዚህ ዙርም ይህንን በማስቀጠል ከ25 ሚሊየን በላይ ወጣቶች በ14 አቅጣጫዎች ተሰማርተው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እንደሰጡ ጠቁመዋል።
በአገልግሎቱ ከ53 ሚሊየን በላይ ዜጎች ተጠቃሚ ይሆናሉ ብለዋል።
አቶ ደስታ ሌዳሞ በበኩላቸው፤ ወሰን ተሻጋሪ የወጣቶች ክረምት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት አብሮነትን የሚያጠናክር ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።
ወጣቶች ሀገራቸውን የሚጠብቁ እና የሚያሳድጉ በመሆናቸው አንድነትን ለሚሸረሽሩ አካሄዶችና ከፋፋይ እሳቤዎች ጆሮ መስጠት እንደሌለባቸው አስገንዝበው፤ እኛነትን በማስቀደም መረዳዳትና መተጋገዝም የምንጊዜም መርሃቸው ማድረግ እንዳለባቸው ተናግረዋል።
በሔብሮን ዋልታው

