አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 1፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ለዓለም ንግድ ድርጅት አባልነት ድርድር ማዕቀፍ ከታይላንድ ጋር የሁለትዮሽ የገበያ መዳረሻ ፕሮቶኮል ተፈራረመች።
ስምምነቱን በጄኔቫ የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ፀጋአብ ክበበው እና በታይላንድ በኩል በዓለም ንግድ ድርጅት እና በዓለም የአዕምሯዊ ንብረት ድርጅት የታይላንድ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ባኦቺትር ፒትፊልድ ተፈራርመዋል።
አምባሳደር ፀጋአብ ክበበው የፕሮቶኮሉ መፈረም በኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባልነት ሒደት ውስጥ ከፍተኛ ዕመርታ መሆኑን መግለጻቸዉን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ አመልክቷል።
ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን ያቀረበችዉ ጥያቄ ለበርካታ ዓመታት በተለያዩ ምክንያች ተጓትቶ በቅርቡ አባል ለመሆን የሚያስችሏት ስራዎች በመጠናቀቃቸው የአባልነት ሂደቱ እየተፋጠነ መሆኑ ይታወቃል።
ለዚህ ሲባል የተቋቋመው ኮሚቴ ከሚሰራቸው ስራዎች መካከል የኢትዮጵያን አባልነት የሚደግፉ ሀገራትን ማበራከት እና የገበያ የሁለትዮሽ ስምምነት መፈራረም ይገኝበታል።
ሚያዚያ ወር ላይ በጄኔቫ በተካሄደው በ7ኛው የሥራ ላይ የቡድን ስብሰባ ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ድል የተገኘበት መሆኑን ይታወሳል፡፡
ለዚህ ድል መገኘት ኢትዮጵያ የተገበረችው የማክሮኢኮኖሚ ማሻሻያ አስተዋጽኦ ከፍተኛ ሲሆን፤ ለ226 የአባል ሀገራት ጥያቄዎች ጥልቅ ምላሾችን የመስጠት፣ የስራ ቡድን ረቂቅ ሪፖርትን የማዳበርና 32 የግዴታ አንቀጾችን ማጠናቀቅን ጨምሮ ከ9 አባላት ጋር የሁለትዮሽ የገበያ ዕድል ድርድሮች ተጠናቅቀዋል።

