አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 1፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በሶማሌ ክልል በግንባታ ላይ የሚገኙ ፕሮጀክቶች በፍጥነትና በጥራት እንዲጠናቀቁ በትኩረት እየተሰራ ነው አሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሃመድ፡፡
የሶማሌ ክልል የ2018 በጀት ዓመት የሴክተር ቢሮዎች የአፈጻጸም ግምገማ መድረክ እየተካሄደ ነው፡፡
አቶ ሙስጠፌ በዚህ ወቅት እንዳሉት ÷ ግንባታ ላይ የሚገኙ ፕሮጀክቶችን በተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ በማጠናቀቅ የክልሉን እድገት ለማፋጠን የሚደረገው የክትትልና ድጋፍ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡
በክልሉ ከለውጡ በፊት የመንገድን ጨምሮ የሌሎች መሰረተ ልማት አቅርቦት ችግር በስፋት ይስተዋል እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
አሁን ላይ ግን ተቋማቱ በራሳቸው አቅም ገቢና ሀብት በማመንጨት የተለያዩ ፕሮጀክቶችን እየገነቡ እንደሚገኙ ነው ያስገነዘቡት፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ የከተሞች መሬት አስተዳደር ሥርዓት ወጥ በሆነ አሠራር እንዲመራ በቁርጠኝነት መሥራት እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
የከተሞችን ዕድገት በሚመጥን መልኩ ለመምራትም የመሬት አስተዳደር ሥርዓቱን በዲጂታል አሠራር ለማጎልበት እንደሚሰራ መጥቀሳቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ወጣቶችን በተለያዩ የሥራ ዘርፎች በማደራጀት ተጠቃሚ ማድረግ የተቻለ ሲሆን ÷ በዚህም ለ174 ሺህ 340 ወጣቶች የሥራ ዕድል መፈጠሩ ተመላክቷል፡፡

