Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ የገነባችው አቅም ዓለም አቀፍ እውቅና አግኝቷል – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 1፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በፋርማሲቲካል እና ሆስፒታል ዘርፎች ላይ ያለው የግንባታና ቁጥጥር አቅም በዓለም የመድኃኒት ቁጥጥር ኤጀንሲ ዕውቅና ተሰጥቶታል አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ምላሽና ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት እንዳሉት፥ በጤናው ዘርፍ ባለፉት ጊዜያት በርካታ ውጤታማ ተግባራት ተከናውነዋል።

ቀደም ሲል 4 በመቶ የነበረው የሀገር ውስጥ የመድኃኒት ማምረት አቅም በአሁኑ ወቅት ከ44 እስከ 45 በመቶ ማደጉን ገልጸዋል።

በፋርማሲቲካል ዘርፍ አጠቃላይ ሀገራዊ አቅምን ለመገንባት የአፍሪካ የጤና ምርምር ኢንስቲትዩትን ጨምሮ ሰፊ የላቦራቶሪ ግንባታዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል፡፡

በአዲስ አበባ ባለፉት ወራት በርካታ የሕክምና ተቋማት መመረቃቸውንና በሚቀጥሉት ወራትም ተጨማሪ ተቋማት ተመርቀው አገልግሎት እንደሚጀምሩ ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያን ሰፊ ፍላጎት በሁለት እና በሦስት ሆስፒታሎች ማሟላት እንደማይቻል የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ የሕክምና ተቋማትን ደረጃ ለማሻሻል በሚቀጥሉት 5 ዓመታት ዓለም አቀፍ ደረጃ የጠበቁ የሕክምና መስጫዎችን መገንባት ዋነኛ ግብ መሆኑን አመልክተዋል።

ከዚህ ጋር በተያያዘ ደግሞ የወባ በሽታን ለመከላከል አጎበር መሠራጨቱንና 3 ሚሊየን የሚጠጉ ቤቶች ጸረ ወባ ኬሚካል መረጨታቸውን ገልጸው፤ ለመጀመሪያ ጊዜ በ58 ወረዳዎች ክትባት መሰጠቱን አብራርተዋል።

በዮናስ ጌትነት

Exit mobile version