በኢትዮጵያ የከተማ ልማት ታሪክ ውስጥ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተጀምሮ ወደ ክልል ከተሞች የተስፋፋው የኮሪደር ልማት የከተሞችን ገፅታ በከፍተኛ ደረጃ እየቀየረው ይገኛል።
ከዚህ ሰፊ የልማት እንቅስቃሴ ጎን ለጎን ደግሞ ወደ ውስጥ ያሉ የመኖሪያ መንደሮችን ደረጃ ለማሻሻል የተጀመረው የተቀናጁ ሞዴል የከተማ ብሎኮች ግንባታ አዲስና ተስፋ ሰጪ ምዕራፍ ከፍቷል።
ይህ አዲስ የከተማ ፕላን አቀራረብ መዲናዋን ዘመናዊ፣ ፅዱ እና ለነዋሪዎቿ ምቹ ከማድረግ ባለፈ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ትስስርን የሚያጠናክሩ ዘላቂ አንደምታዎችን ይዟል።
በተለምዶ የከተማ ማደስ ስራዎች ሲነሱ የነባር ነዋሪዎች መፈናቀል እና የማህበረሰብ ስነ-ልቦናዊ መበተን ቀዳሚው ስጋት ነበር።
የሞዴል የከተማ ብሎኮች ልማት ግን ይህንን አካሄድ የቀየረ ነው።
ነዋሪዎች ከአካባቢያቸው ሳይነሱ፣ ባሉበት መንደር ውስጥ ያሉትን መኖሪያ ቤቶች፣ የጋራ መገልገያዎችን እና የውስጥ መንገዶችን በጋራ በማልማት ላይ ያተኩራል።
ይህም ማህበረሰቡ ለዘመናት ያካበተው ማህበራዊ እሴት ሳይቋረጥ የኑሮ ደረጃው እንዲያሻሽል ያስችለዋል።
ይህ የልማት ሞዴል የመኖሪያ እና የንግድ ቦታዎችን በአንድ ላይ አጣምሮ የያዘ ነው።
አብዛኛዎቹ የከተማዋ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ነዋሪዎች ህይወታቸው የተመሰረተው በአነስተኛ ንግድ እና በቤት ውስጥ ስራዎች ላይ ነው።
ብሎኮቹ የንግድ ሱቆችን፣ የአነስተኛ ማኑፋክቸሪንግ ቦታዎችን እና የገበያ ማዕከላትን በውስጣቸው ስለሚያካትቱ፣ ነዋሪዎች የተሻሻለ የመኖሪያ ቤት ማግኘታቸው ብቻ ሳይሆን የገቢ ምንጫቸውም ተጠብቆ እንዲቀጥል ያደርጋል።
ይህ ደግሞ በከተማዋ ያለውን ድህነት ለመቀነስ ትልቅ አስተዋፅዖ ያበረክታል።
የሞዴል ብሎኮች ግንባታ የነዋሪዎችን የዕለት ተዕለት የኑሮ ደረጃ የሚያሻሽሉ በርካታ መሠረተ ልማቶችን ያካትታል።
ብሎኮቹ ለህፃናት መጫወቻ፣ ለአረጋውያን ማረፊያ እና ለስፖርት ማዘውተሪያ የሚሆኑ ስፍራዎችን ያካትታሉ።
ደረጃቸውን የጠበቁ የውስጥ ለውስጥ አስፋልት እና የኮብልስቶን መንገዶች፣ የፍሳሽ ማስወገጃ መስመሮች እና ወጥ የቆሻሻ አያያዝ ስርዓቶችም አሉት።
በተጨማሪም የማኅበረሰብ አቀፍ ፖሊስና የጥበቃ ማዕከላትን በማካተት የአካባቢውን ሰላም አስተማማኝ እያደረገው ነው።
ሌላው የዚህ ሞዴል ትልቁ አንደምታ ከፍተኛ፣ መካከለኛ እና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች በአንድ ላይ ማስተናገዱ ነው።
በብሎኮቹ ውስጥ የሚገነቡት ህንጻዎች እና የንግድ ቦታዎች የሚያስገኙት ገቢ፣ የዝቅተኛ ገቢ ማህበረሰብ ክፍሎችን የመኖሪያ ቤት ግንባታ እና የመሠረተ ልማት ወጪን ለማቃለል ይውላል።
ይህ አካሄድ የከተማዋን የቤት አቅርቦት ችግር በዘላቂነት ለመፍታት እና ፍትሃዊ የከተማ ልማትን ለማረጋገጥ ትልቅ የፖሊሲ መፍትሄ እየሆነ ነው።
የእነዚህ ብሎኮች ስኬት በዋናነት የመንግስት፣ የባለሀብቶች እና የነዋሪዎች የተቀናጀ ተሳትፎ ውጤት ነው።
በብሎኮቹ ህብረተሰቡ በጉልበቱ፣ በገንዘቡ እና በሃሳቡ ልማቱን በባለቤትነት እንዲመራው እየተደረገ ይገኛል፡፡
ይህ ሂደት በማህበረሰቡ ውስጥ የባለቤትነት ስሜትን ከመፍጠሩም በላይ፣ የጋራ ችግሮችን በጋራ የመፍታትና የበጎ ፈቃድ ባህልን በከፍተኛ ደረጃ እያሳደገው ነው፡፡
በአጠቃላይ፣ የአዲስ አበባ ሞዴል የከተማ ብሎኮች ልማት መዲናዋን ወደ ዓለም አቀፍ ስታንዳርድ ከማሸጋገር ባለፈ፣ የነዋሪዎቿን ማህበራዊ ህይወት እና የኢኮኖሚ አቅም ባገናዘበ መልኩ የሚተገበር ፍትሃዊ የከተማ ማደስ ስራም ነው።
ሥራው በስፋት ወደ ሀገሪቱ ትላልቅ ከተሞች ሲሰፉ፣ የኢትዮጵያን የከተማ ልማት ጉዞ ወደ አዲስ ከፍታ እንደሚያሸጋግረው አያጠራጥርም፡፡

