አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 2፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢትዮጵያ በጠመንጃ አፈሙዝ ሥልጣን ለመያዝ መሞከር ጊዜው ያለፈበት ኋላቀር እሳቤ ነው አሉ የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን) ምክትል ሊቀመንበር መልካሙ ፀጋዬ።
በኢትዮጵያ ባለፉት ጥቂት ዓመታት የፖለቲካ ስርዓት አካታችና አሳታፊ መሆኑን ጠቅሰው፥ በሀገር ጉዳይ ላይ ሁሉም በእኩልነት የሚሳተፍበት ምቹ የፖለቲካ ምህዳር ተፈጥሯል ብለዋል።
አጋር ተብለው የዳር ተመልካች የነበሩ ክልሎች አሁን ላይ እኩል ተሳታፊ ሆነው በሀገራቸው ጉዳይ ላይ እየወሰኑ ሲሆን፥ በውጭና በሀገር ውስጥ በትጥቅ ትግል ውስጥ የነበሩ አካላት በለውጡ በተፈጠረው ምቹ መደላድል በሰላማዊ ትግል ቀጥለዋል ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ በዴሞክራሲያዊ ምርጫ ጠንካራ ሀገረ መንግሥት የመገንባት ሒደት ላይ መሆኗን ገልጸው፥ እነዚህን መልካም እድሎች በመግፋት በጠመንጃ መልስ ለማግኘትና ሥልጣን ለመያዝ መሞከር አክሳሪ አካሄድ ነው ብለዋል፡፡
በምክክር ችግሮችን የመፍታትና በምርጫ የማሸነፍ ሰፊ እድል እያለ በጫካ የሚደረግ የጠመንጃ እንቅስቃሴ በፍፁም ተቀባይነት እንደሌለው ፓርቲያችን በፅኑ ያምናል ነው ያሉት።
በተቃርኖ የከረሩ ዋልታ ረገጥ እሳቤዎችን በማለዘብና በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገኘውን ሀገራዊ የምክክር እድል በመጠቀም ዘላቂ መፍትሄ ማምጣት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
ለሀገራዊ ምክክሩ የተለዩ አጀንዳዎች የዜጎችን የዘመናት ጥያቄዎች ማዕከል ያደረጉ በመሆናቸው ሁሉም ለስኬታማነቱ ሊሰራ ይገባል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

