Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ክልሉ 8 ሺህ 985 ኪሎ ግራም ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ ላከ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 2፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል 8 ሺህ 985 ኪሎ ግራም ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ ተልኳል አለ የክልሉ ማዕድን ሃብት ልማት ቢሮ፡፡

የቢሮው ኃላፊ አቶ ቱጃኒ አደም እንዳሉት÷ በ2018 በጀት ዓመት የወርቅ ምርትን ለማሳደግ በተከናወነው ዘርፈ ብዙ ሥራ ተጨባጭ ውጤት ተገኝቷል፡፡

በዚህ መሰረትም በዓመቱ 8 ሺህ 985 ኪሎ ግራም ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ መላኩን ለፋና ዲጂታል ተናግረዋል፡፡

ለተገኘው ስኬት መንግሥት በዘርፉ የወሰደው የፖሊሲ ማሻሻያ ለአምራቾች የፈጠረው ምቹ ሁኔታ ቀጥተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል ነው ያሉት፡፡

የወርቅ ምርት ለክልሉ የገቢ አቅም መጠናከር ጉልህ ሚና እየተጫወተ መሆኑንና በበጀት ዓመቱ ቢሮው ከ246 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ ማግኘቱን ገልጸዋል።

በዘርፉ የሚስተዋለውን ሕገ ወጥ ንግድ ለመከላከል በትኩረት መሰራቱን ጠቁመው÷ በዚህም 100 በላይ ባለሃብቶችና ነጋዴዎች ላይ ርምጃ መወሰዱን አመልክተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሰሞኑን ለሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት አባላት በሰጡት ማብራሪያ ፥ ኢትዮጵያ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ከወርቅ ማዕድን 5 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር ታሪካዊ ገቢ ማስመዝገቧን ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡

Exit mobile version