አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 2፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ለኢንቨስትመንት፣ ለንግድና ለቀጣናዊ ደህንነት መረጋገጥ ቁልፍ ስትራቴጂያዊ ጠቀሜታ ያላት ሀገር ናት አሉ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች።
በኢትዮጵያ የሮማኒያ አምባሳደር ጁሊያ ፓታኪ እንደገለጹት÷ ኢትዮጵያ በቀጣናው ኢኮኖሚያዊ ውህደት እንዲሳለጥ እንዲሁም ሰላምና ደህንነት እንዲጠበቅ የሚደነቅ ሚና እየተጫወተች ነው።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ፈጣን ዕድገት እያስመዘገቡ ካሉ ሀገራት ግንባር ቀደም መሆኗን አውስተው÷ ነፃ ንግድ እና የገበያ ትስስር በአህጉሪቱ ያለውን የኢኮኖሚ ልማት ለማፋጠን አስፈላጊ መሆናቸውን አመልክተዋል።
አዲስ አበባ የአፍሪካ ሕብረት መቀመጫ መሆኗ እና ታሪካዊ ሚናዋ ኢትዮጵያን ለዲፕሎማሲ እና የአፍሪካን ተግዳሮቶች ለመፍታት በሚደረጉ የጋራ ጥረቶች ተመራጭ ሀገር እንዳደረጋት አብራርተዋል።
በኢትዮጵያ የኦማን ሚሲዮን መሪ የሆኑት አፍካር አል ፋርሲ በበኩላቸው÷ ኢትዮጵያ ባላት ሰፊ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥና በማደግ ላይ ባለው ኢኮኖሚዋ ሳቢያ በቀጣናው ወሳኝ ሀገር ናት ብለዋል።
ቀጣናውን የማስተሳሰር አህጉራዊ ሚናዋ እያደገ ነው ያሉት ሚሲዮን መሪው÷ በአፍሪካ ግዙፉ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለቀጣናዊ እና ለአህጉራዊ ውህደት ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳለው ጠቁመዋል።
በንግድና በኢንቨስትመንት ዙሪያ የኢትዮጵያ እና የኦማን የሁለትዮሽ ግንኙነት እየጎለበተ መምጣቱን ጠቅሰው÷ በሀገራቱ መካከል ያለውን የንግድ ልውውጥ ይበልጥ በማስፋት የሁለትዮሽ ግንኙነቱን ለማሳደግ ፍላጎት መኖሩን ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ በሪል ስቴት እና መሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች፣ በአምራች፣ በኮንስትራክሽንና በግብርና ዘርፎች የኦማን ባለሃብቶች ሊሰማሩባቸው የሚችሉባቸው ሰፊ የኢንቨስትመንት አማራጮች አሉ ማለታቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።

