አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 2፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ሕገ ወጡ የሕወሓት ቡድን የትግራይ ክልል ተተኪ ትውልድን ሆን ብሎ በመዋቅራዊ አሰራር እያጠፋና እያመከነ ነው አሉ የስምረት ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የምክር ቤት አባል ኬርያ ኢብራሂም።
ኬርያ ኢብራሂም እንዳሉት ÷ ሕገ ወጡ የሕወሓት ቡድን “ፅምዶ” በሚል ስያሜ ከሻዕቢያ እና ከሀገር ውስጥ ፅንፈኛ ኃይሎች ጋር በመጣመር ኢትዮጵያን ለማተራመስ እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡
ቡድኑ የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት እያጣቀሰ ለዳግም ጦርነት ጊዜ መግዣነት በመጠቀም የትግራይ እናቶችን እያስለቀሰ እንደሚገኝ በአጽንኦት ተናግረዋል፡፡
የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት የጥይት ድምፅ በማጥፋት ለክልሉ ሕዝብ ተስፋ የሰጠ የሰላም በር እንደነበር አስታውሰው÷ የፌዴራል መንግሥት በስምምነቱ መሠረት የክልሉ ሕዝብ የተረጋጋና ሰላማዊ ሕይወት የሚመራበትን ዕድል እንደፈጠረ ጠቁመዋል።
ሕገ ወጡ የሕወሓት ቡድን ግን ለትግራይ ሕዝብ ትልቅ እፎይታን ይዞ የመጣውን ስምምነት ለጊዜ መግዣነት በመጠቀም የክልሉን ጊዜያዊ አስተዳደር በማፍረስ በጨረባ ምርጫ ያደራጀውን ሕገወጥ ም/ቤት በመሰብሰብ ተቀባይነቱን ያጣ ካቢኔ ማዋቀሩን አስረድተዋል።
ከሻዕቢያ ጋር ከሚፈጽመው የወርቅና የከበሩ ማዕድናት ምዝበራ ባሻገር፣ የትግራይ ወጣቶችን ለሱዳን ጦርነት በመሸጥ የውጭ ምንዛሪ ገቢን የጦር መሣሪያ መግዣ በማድረግ የክልሉን ሕዝብ ወደ ባሰ ጥፋት እየመራው እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
በአሁኑ ወቅት ሕገወጡ ሕወሓት የትግራይ ክልል ተተኪ ትውልድን ሆን ብሎ በመዋቅራዊ አሰራር እያጠፋ መሆኑን ገልጸው÷ በተለይም ራሱን ለዳግም ጦርነት በማዘጋጀት ሕፃናትን ከእናታቸው ጉያ በመንጠቅ የትግራይ እናቶችን የደም እምባ እያስለቀሰ ይገኛል ነው ያሉት፡፡
ቡድኑ ከሀገር ውስጥና ከውጭ የጠላት ኃይሎች ጋር ያልተቀደሰ ጋብቻ በመፍጠር፣ የትግራይ ክልል ሕዝብን ለዳግም ጉስቁልና ለማመቻቸት ጥረት እያደረገ ነው ያሉት ኬርያ ኢብራሂም ÷ በፍጹም ጭካኔ ሕፃናትን ወደ ጦር ካምፕ በማጋዝ ሰብዓዊ ግፍ እየፈጸመ መሆኑን ገልጸዋል።
የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተናንም “እራሴ አዘጋጃለሁ” በሚል፣ የወጣቱን የነገ ተስፋና ሕልም እያጨለመ መሆኑን ጠቅሰው÷ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የዓለም አቀፍ ተቋማትና ሀገራት የቡድኑን እኩይ ሴራ እንዲታገሉ ጥሪ ማቅረባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

