አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 2፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከሕገ ወጥ ነዳጅ ንግድ ጋር በተያያዘ ከ350 በላይ ማደያዎች ላይ ርምጃ ተወስዷል አለ የነዳጅና ኢነርጂ ባለስልጣን ፡፡
የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ደስታው መኳንንት (ዶ/ር) ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን እንዳሉት ÷ በዓመቱ 4 ነጥብ 5 ሚሊየን ሜትሪክ ቶን ነዳጅ ለማቅረብ ታቅዶ 4 ነጥብ 2 ሚሊየን ሜትሪክ ቶን በማቅረብ የዕቅዱን 94 በመቶ ማሳካት ተችሏል፡፡
በዚህም የነጭ ናፍታ ሥርጭት ለማደያዎችና ለክልል 69 ነጥብ 5 በመቶ ፣ ለቁልፍ ፕሮጀክቶች 9 ነጥብ 5 በመቶ እንዲሁም ለመንገድ ፕሮጀክቶች 13 በመቶ ፣ ለኢንዱስትሪ 7 በመቶ እና ለግብርና 1 በመቶ ድርሻ እንዳላቸው አንስተዋል።
በሆርሙዝ ሰርጥ መዘጋት ምክንያት የተፈጠረውን የነዳጅ ቀውስ መንግሥት የተወጣበት መንገድ ተሞክሮ ሊሆን የሚችል ነው ሲሉ አውስተዋል ዳይሬክተሩ፡፡
የተፈጠረውን ጫና እንደ መልካም አጋጣሚ በመውሰድ በሕገ ወጥ ተግባራት ላይ ተሰማርተው የነበሩ 688 ግለሰቦችን በሕግ ተጠያቂ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል፡፡
ከሕገ ወጥ ነዳጅ ንግድ ጋር በተያያዘ ከ350 በላይ ማደያዎች ላይ የተለያየ ርምጃ መወሰዱን ጠቁመው ÷ መዳረሻቸውን የቀየሩ ቦቴዎች እስከ 6 ወር ለሚደርስ ጊዜ መታገዳቸውን ተናግረዋል፡፡
በነዳጅ ላይ ያለውን ጥገኝነት ለመቀነስ የተፈጥሮ ጋዝን ወደ ሥራ ለማስገባት እየተሰራ ሲሆን ÷ ለአከፋፋዮች ፈቃድ መስጠት፣ የተፈጥሮ ጋዝን የሚጠቀሙ ኢንዱስትሪዎችንና ተሽከርካሪዎችን የመለየት ሥራ መከናወኑን አመልክተዋል፡፡
በዚህ መሰረትም የተፈጥሮ ጋዝን የሚያከፋፍሉ ሶስት ማደያዎች ግንባታ መከናወኑን ነው የጠቆሙት፡፡
በመሳፍት እያዩ

