Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የገጠር ኮሪደር ለአርሶ አደሩ የኑሮ ዘይቤ መሻሻል…

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 3፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢትዮጵያ የተጀመረው የኮሪደር ልማት ከተሞችን ዘመናዊ፣ ውብ፣ ጽዱና ለኑሮ ምቹ ከማድረግ አንጻር ያሳየው እመርታ የሚደነቅ ነው፡፡
ከተሞች ዘመኑን የዋጁ ይሆኑ ዘንድ በአዲስ አበባ የተጀመረው የኮሪደር ልማት ሥራ አሁን ላይ በሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡
በተመሳሳይ በገጠር አካባቢ የሚኖር የዜጎችን ሕይወት በተሟላ መልኩ ለመቀየር እየተከናወነ የሚገኘው የገጠር ኮሪደር ልማት ሥራ አበረታች ነው፡፡
በኢትዮጵያ አብዛኛው የሕብረተሰብ ክፍል የኑሮ መሰረቱ በገጠር አካባቢዎች ሲሆን ÷ የገጠር ኮሪደር ልማትም በእነዚህ አካባቢዎች የሚኖሩ የሕብረተሰብ ክፍሎችን የኑሮ ዘይቤ ለማሻሻልና ወደ ዘመናዊነት ለማምጣት ያለመ ነው፡፡
የገጠር ኮሪደር ልማት በገጠሪቱ የኢትዮጵያ ክፍሎች ላይ ትኩረት በማድረግ ለማሕበረሰቡ ዘመናዊ የአኗኗር ሥርዓትን የሚያላብስ ፣ ውብና ጽዱ የመኖሪያ አካባቢ ውስጥ የመኖር ዕድልን የሚፈጠር ከመሆኑ ባሻገር የዜጎችን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል ሚናው ትልቅ ነው፡
የገጠር ኮሪደር ልማት የሕብረተሰቡን የአኗኗር ዘዬ በማሻሻል፣ የአርሶ አደሩን ጤና በመጠበቅ እንዲሁም ዘመናዊነትን በማንጸባረቅ ከተሜነትን ወደ ገጠር ያመጣል።
በገጠር ኮሪደር የሚሰሩ ሞዴል መንደሮች በአካባቢው በሚገኙ ግብዓቶች የሚገነቡ በመሆናቸው አርሶ አደሩ በቀላሉ በመተግበር ጤናማ እና ክብር ያለውን ሕይወት እንዲኖር ያስችላሉ፡፡
የገጠር ኮሪደር ልማት ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ እና ሥነ ምህዳራዊ ፋይዳን ጨምሮ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለው ሲሆን ÷ ይህም ዘላቂ ልማትና የተረጋጋ ሕብረተሰብ ለመፍጠር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል።
ከለውጡ በፊት የኢኮኖሚ ምንጭ የሆነው የገጠሩ አካባቢ ትኩረት ተነፍጎት የቆየ በመሆኑ የተሻለ ኑሮን ፍለጋ ወደ ከተማ የሚሄደው ወጣት ቁጥር ከፍተኛ ነበር፡፡ዛሬ ላይ በሚኖርበት አካባቢ ተረጋግቶ እሴት መጨመር ላይ እየሰራ እንዲኖር የሚያስችል ሁኔታ መፍጠር ተችሏል።
የገጠር ኮሪደር በውጤት ደረጃ የሕብረተሰብ ሽግግርን የሚያመጣ እና የመሰረተ ልማትን ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ ጉዳዮችን ያቀፈ ነው፡፡ በገጠር አካባቢዎች ዘመናዊ አኗኗርን የሚፈጥር እና የአርሶ አደሩን ሕይወት የሚቀይር ሀገራዊ ውጥንም ነው ።
በጥቅሉ የገጠር ኮሪደር ልማት አርሶ አደሩ የቴክኖሎጂ ተጠቃሚና ዘመናዊ ስልተ-ምርት እንዲከተል የሚያደርግ አዲስ የአኗኗር ባሕልን የሚተክል ሲሆን ÷ እንደሀገር የከተማ ፍልሰትንና የምግብ ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ ምቹ ዐውድን ይፈጥራል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንዳሉት÷ በከተማ ላይ የተሰራው ሥራ ወደ ገጠር ካልመጣ በስተቀር በከተማ ብቻ ተሰርቶ የተሟላ ብልጽግናን ማረጋገጥ አይቻልም፤ ገጠሩን መቀየር ያስፈልጋል፤ ለዚህ ደግሞ የገጠር ኮሪደር ዋነኛ መሳሪያ ነው ፡፡
እያንዳንዱ የማሕበረሰብ ክፍል የሚገባውን አይነት ኑሮ እንዲኖር ማስቻልን የገጠር ኮሪደር ልማት አላማው አድርጎ መነሳቱን ጠቅሰው÷ ኢኒሼቲቩ በገጠሩ አካባቢ ሰዎች ከእንስሳት ጋር በጋራ ይኖሩ የነበረበትን ተገቢ ያልሆነ መንገድ እያስቀረ ነው ብለዋል፡፡
በእርግጥ ለአርሶ አደሩ እንስሳት እጅግ አስፈላጊዎች ናቸው፤ ለዚህም የገጠር ኮሪደር ለእንስሳት የተለየ ቦታን ያመቻቸ መሆኑ የማሕበረሰቡን ጤና ከመጠበቅ አንጻርና ለሕክምና የሚወጡ አላግባብ ወጪዎችን በማስቀረት ጉልህ ድርሻውን እየተወጣ ነው፡፡
የገጠሩን ማህበረሰብ የአኗኗር ባሕል ከግምት ያስገባና ለእንስሳት እርባታ አመቺ ሁኔታን የፈጠረ ከመሆኑ ባሻገር ከእንስሳቱ በሚገኘው ተረፈ ምርት የባዮ ጋዝ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያስችላል፡፡
ይህም እናቶች በእንጨት ለቀማ የሚደክሙትን ድካም በማስቀረት ሸክማቸውን በማቅለል ከብዙ እንግልት እና ስቃይ እንዲያርፉ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል፡፡
በሌላ በኩል የሶላር ኃይልን ያካተተ በመሆኑ ኢትዮጵያ ያሰበችውን የታዳሽ ኃይል አቅርቦት በተግባር የሚያረጋግጥና ማህበረሰቡ ከሌሎች አካባቢዎች ጋር በቀላሉ መገናኘት እንዲችል ዕድል የፈጠረ ነው፡፡
የገጠር ኮሪደር ልማት የሕብረተሰብ ሽግግርን የሚያሳልጥና የመሰረተ ልማት ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ በመሆኑ መንግሥት፣ ባለሃብቶች እና አጋር አካላት በትብብር በመስራት ሊያጠናክሩት ይገባል፡፡
በቤተልሔም ግርማ

Exit mobile version