አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 3፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት አማካኝነት እየተሰጠ ባለው የጤና አገልግሎት በርካታ ዜጎች ተጠቃሚ እየሆኑ ነው አሉ፡፡
ሚኒስትሯ ‘ኸርት አታክ ኢትዮጵያ’ ከቅዱስ ጴጥሮስ ሆስፒታል ጋር በመተባበር እየሰጠ ያለውን ነጻ የልብ ቀዶ ሕክምና አገልግሎት ተመልክተዋል።
በምልከታቸው ወቅት እንደገለጹት፤ አገልግሎቱ የልብ ቀዶ ሕክምና በመጠባበቅ ላይ የሚገኙ ህሙማንን ቁጥር በመቀነስና ሕይወትን በማትረፍ ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከተ ይገኛል።
በመላ ሀገሪቱ የሚሰጡ የበጎ ፈቃድ የጤና አገልግሎቶች የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ እያደረጉ እንደሆነ ገልጸዋል።
በዚህም ነጻ ሕክምና፣ የደም ልገሳ እና የህክምና መሳሪያዎች ጥገናን ጨምሮ አስፈላጊ አገልግሎቶችን የማድረስ ስራ መጠናከሩን አመልክተዋል።
የኸርት አታክ ኢትዮጵያ አስተባባሪ ዶ/ር ተስፋዬ ተሊላ በበኩላቸው ቡድኑ በአንድ ሳምንት ውስጥ ለ34 ህሙማን የልብ ቀዶ ሕክምና በማድረግ ሕይወት አድኗል ብለዋል።
የጤና ሚኒስትሯ ለሆስፒታሉ ሰራተኞች እና በበጎ ፈቃድ ነጻ የልብ ቀዶ ሕክምና እየሰጡ ለሚገኙት ቡድን አባላት ላበረከቱት አገልግሎትና ላተረፉት ሕይወት ምስጋና አቅርበዋል።

