አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 3፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ለቃለ ጉባኤ ያዦች ሥልጠና እየተሰጠ ነው።
በሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ወቅት የቃለ ጉባኤ ያዦች ሚና ወሳኝ ነው ያለው ኮሚሽኑ፤ ቃለ ጉባኤ ያዦች የምክክር ነጥቦችን፣ አስተያየቶችን እና ምክረሀሳቦችን የመመዝገብ ሚና እንዳላቸው ገልጿል።
በተጨማሪም የውሳኔ ሀሳቦችን እና የስምምነት ነጥቦችን ለይቶ ማስቀመጥም የቃለ ጉባኤ ያዦች ኃላፊነት ነው።
ይህንኑ ከግምት በማስገባት የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከ11 ክልሎች እና ከሁለት ከተማ አስተዳደሮች ለተወጣጡ የምክክር ቃለ ጉባኤ ያዦች የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሐግብር አዘጋጅቷል።
የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መሥፍን አርአያ፤ የምክክር ሂደቱ ሰፊና ግዙፍ መኾኑን ጠቅሰው፤ ቃለ ጉባኤ ያዦች ትልቅ አበርክቶ እንዳለቸው ገልጸዋል።
ቃለ ጉባኤ ያዦች የምክክር ሂደቱን ግልጽነት እና ተዓማኒነት በማረጋገጥ ወሳኝ ሚና እንዳላቸው የጠቀሱት ዋና ኮሚሽነሩ፤ የውይይቶች ውጤት በትክክልና በገለልተኝነት እንዲመዘገብ ከፍተኛ ሙያዊ ኃላፊነት እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።
በውይይቱ ወቅት በምክክር ቃለ ጉባኤ አያያዝ ሂደት፣ በሰነድ አዘገጃጀት፣ በመረጃ ጥራት እና በሥነ ምግባር ዙሪያ ሰፊ ውይይት የተደረገ ሲሆን፤ ተሳታፊዎችም ጥያቄዎቻቸውንና አስተያየቶቻቸውን አቅርበው በኮሚሽኑ ባለሞያዎች ምላሽ ተሰጥቷቸዋል።
በግንዛቤ ማስጨበጫ መርሐግብሩ ላይ ከዩንቨርሲቲዎች፣ ከፍርድ ቤቶች፣ ከሲቪክ ማኅበራትና በግለሰብ ውክልና የተመረጡ ከ180 በላይ ቃለ ጉባኤ ያዦች ተገኝተዋል።

