Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር፣ የምግብ ዋስትናው የተረጋገጠ ማህበረሰብ ለመገንባት…

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 3፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት የተጀመረው የሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር ኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናን እንድታረጋግጥ የሚያስችል ሀገራዊ ትልም ነው፡፡

ኢትዮጵያ እልፍ የተፈጥሮ ፀጋን የታደለች ሀገር ስትሆን፤ በተለይም ለምግብነት የሚውሉ የእንስሳትና የእፅዋት ሀብቶቿ በአህጉርም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተጠቃሽ ያደርጋታል፡፡

በሕዝቡ ዘንድ የነበረው የሥነ ምግብ ልምምድ እንዲሁም ለዘርፉ የተሰጠው አናሳ ትኩረት ከእነዚህ ሀብቶች የሚገኘውን ጥቅም በአግባቡ ተቋዳሽ እንዳትሆን አድርጓት ቆይቷል፡፡

ሀገር የተሰጣትን ጸጋ በሚፈለገው መጠን ካለማች የእንስሳትና የእጽዋት ተዋጽኦ ምርቶች የቅንጦት ምግቦች ሳይሆኑ ከዕለት ማዕድ የማይጠፉ መሰረታዊ ምግቦች እንደሚሆኑ ይታመናል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በ2015 ዓ.ም መርሐ ግብሩን ባስጀመሩበት ወቅት፤ የሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር አርሶ አደሩን፣ አርብቶ አደሩን እና ሸማቹን የሚያገናኝ ድልድይ ነው ብለው ነበር፡፡

በአጠቃላይ በምግብ ራስን መቻል ከሀገር ሉዓላዊነትና ክብር ጋር ጥብቅ ቁርኝት እንዳለው ማንሳታቸው ይታወሳል፡፡

ከምግብ ዋስትና ባሻገር የሥራ ዕድል ፈጠራን በማበረታታት የወጪ ንግድ ገቢን እንደሚያሳድግና ከውጭ የሚገባ የእንስሳት ተዋጽኦን በሀገር ውስጥ እንደሚተካ የታመነበት ተግባር ነው፡፡

መርሐ ግብሩ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ በተሰሩ ሥራዎች የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት በከፍተኛ ሁኔታ እያጠናከረው ይገኛል፡፡

መርሐ ግብሩ በወተት፣ እንቁላል እና ዶሮ እርባታን ጨምሮ በተለያዩ ዘርፎች ምርታማነት እንዲሰፋ በማድረግ ተጨባጭ ውጤት እያስገኘ መጥቷል፡፡

የወተት ምርት አቅርቦት መርሐ ግብሩ ጅማሮውን ሲያደርግ 7 ነጥብ 1 ቢሊየን ሊትር የነበረ ሲሆን፣ አሁን ላይ ወደ 15 ነጥብ 2 ቢሊየን ሊትር ከፍ ብሏል፡፡

የዓሳ ምርት ከአራት ዓመት በፊት ከነበረው 78 ሺህ ቶን ወደ 307 ሺህ ቶን እንዲሁም በዶሮ እርባታ 26 ሚሊየን የነበረው የጫጩት ሥርጭት ወደ 184 ሚሊየን ማድረስ ተችሏል፡፡

በተመሳሳይ በዚህ ዓመት ብቻ ከዚሁ መርሐ ግብር 428 ሺህ ቶን የማር ምርት ተሰብስቧል፡፡

ይህ የሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር ሥርዓተ ምግብን ከማሻሻል ባለፈ ለአርሶ አደሩ ማህበረሰብ እንዲሁም ለከተማ ግብርና ተሳታፊዎች ተጨማሪ የገቢ ምንጭ በመፍጠር የቤተሰብ ኢኮኖሚን እያሳደገ ነው፡፡

የሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር ጤናው የተጠበቀ፣ የምግብ ዋስትናው የተረጋገጠና ኢኮኖሚው የተሻሻለ ማህበረሰብ ለመገንባት የተወጠነ ትልም ነው፡፡

በመልካም ፈቃዱ

Exit mobile version