Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ህይወትን ያቀለለው ዲጂታል ኢትዮጵያ

የዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂ እና ተከታታይ የቴክኖሎጂ ማሻሻያዎች የኢትዮጵያውያንን የዕለት ተዕለት ኑሮ በከፍተኛ ደረጃ እየቀየሩት ይገኛሉ።

ቀደም ሲል ለቀናት ይሰለፍባቸው እና በርካታ እንግልት ይደርስባቸው የነበሩ ህዝባዊ እና ንግድ ነክ አገልግሎቶች ዛሬ በሞባይል ስልክ እና በኢንተርኔት አማካኝነት በደቂቃዎች ውስጥ እየተከናወኑ ነው።

ይህ የዲጂታል ሽግግር የዜጎችን ጊዜ፣ ጉልበት እና ገንዘብ በመቆጠብ ህይወትን እያቀለለ ነው።

በኢትዮጵያ የዲጂታል ክፍያ ስርዓት መዘርጋቱ በኪስ ጥሬ ገንዘብ የመያዝን አስፈላጊነት አስቀርቷል።

እንደ ኢትዮ ቴሌኮም ቴሌብር፣ የሳፋሪኮም ኢምፔሳ እና የባንኮች የሞባይል መተግበሪያዎች ክፍያዎችን እጅግ ፈጣን አድርገውታል።

የውሃ፣ የኤሌክትሪክ፣ የትራፊክ ቅጣት፣ የትምህርት ቤት ክፍያዎች እና የትራንስፖርት ታሪፎች በቤት ውስጥ ሆኖ መክፈል ተችሏል።

መደበኛ ባንክ መሄድ ሳይጠበቅባቸው ዜጎች በስልካቸው ብድር ማግኘት እና መቆጠብ የሚችሉባቸው ዲጂታል መድረኮች ተስፋፍተዋል።

መንግስታዊ አሰራሮችን ወደ ቴክኖሎጂ ማሸጋገሩ ቢሮክራሲን እና ሙስናን በመቀነስ ረገድ ትልቅ ለውጥ አምጥቷል።

ፓስፖርት ማውጣት እና ማደስ፣ የልደት እና ጋብቻ ምስክር ወረቀቶች፣ እንዲሁም የንግድ ፈቃድ ምዝገባ እና እድሳት በኢንተርኔት በኦንላይን የሚከናወኑ ሆነዋል።

የብሄራዊ ዲጂታል መታወቂያ ስርአት እያንዳንዱ ዜጋ አንድ ወጥ እና አስተማማኝ መታወቂያ እንዲኖረው በማድረግ የባንክ፣ የቴሌኮም እና የሌሎች ማህበራዊ አገልግሎቶች ምዝገባን እጅግ አሳልጦታል።

ዲጂታል ኢኮኖሚው ለአዳዲስ ስራ ፈጣሪዎች እና ለተጠቃሚዎች ሰፊ የገበያ እድሎችን ፈጥሯል።

በትራንስፖርት ዘርፍ እና ሌሎች የታክሲ መተግበሪያዎች የከተማ ውስጥ እንቅስቃሴን ደህንነቱ የተጠበቀ እና ምቹ አድርገውታል።

ምግብ፣ አልባሳት እና የቤት እቃዎችን በኦንላይን አዝዞ ያሉበት ቦታ ድረስ ማስመጣት የዘመኑ የኢ-ኮሜርስ መስፋፋት ህይወትን አቅልሏል፡፡

ወጣቶች ባሉበት ሆነው በኢንተርኔት አማካኝነት ለሀገር ውስጥ እና ለዓለም አቀፍ ኩባንያዎች የመስራት እድላቸውን አስፍቷል።

ዲጂታል ኢትዮጵያ ከቅንጦት ባለፈ የማህበረሰባችንን የኑሮ ደረጃ የሚያሻሽል ወሳኝ ጉዳይ ሆኗል።

ቴክኖሎጂን በአግባቡ መጠቀም ስራዎችን ፈጣን፣ ግልጽ እና ወጪ ቆጣቢ እያደረገ ነው፡፡

ሂደቱን ይበልጥ ስኬታማ ለማድረግ የኢንተርኔት ተደራሽነትን ማሳደግ፣ የኔትወርክ ጥራትን አስተማማኝ ማድረግ እና የዜጎችን የዲጂታል እውቀት ማጎልበት ላይ መንግሥት በትኩረት እየሰራ ይገኛል፡፡

Exit mobile version