አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 4፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የጅማ የዓይን ባንክ የዓይን ብሌን ንቅለ ተከላ ለማከናወን ሰዎች በሕይወት እያሉ የዓይን ብሌናቸውን እንዲለግሱ ጥሪ አቅርቧል፡፡
የጅማ የዓይን ባንክ የዓይን ብሌን ልገሳ የንቅናቄ መድረክ በጅማ ከተማ አካሄዷል፡፡
የጅማ ዩኒቨርስቲ የዓይን ሕክምና ትምህርት ክፍል ሃላፊና የጅማ አይን ባንክ ሜዲካል ዳሪክተር ዶ/ር ጃፈር ከድር በዚህ ወቅት ÷ በሀገር አቀፍ ደረጃ የአይን ሕክምና የሚፈልጉ ከ500 ሺህ በላይ ሰዎች መኖራቸውን አንስተዋል፡፡
በዘንድሮው ዓመት የጅማ የዓይን ባንክ ለ40 ሰዎች የዓይን ብሌን ንቅለ ተከላ ማከናውኑን ገልጸው÷የዓይን ብሌን ለማከም የዓይን ብሌን ለጋሾች እንደሚያስፈልጉ ተናግረዋል።
በጅማ እና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ አካባቢ የዓይን ብሌን ሕክምና ለሚጠባበቁ ሰዎች ለመድረስ የዓይን ብሌን ለጋሾች ያስፈልጋሉ ነው ያሉት፡፡
የሆስፒታሉ የክሊኒካል ዳይሬክተር ዶ/ር ሁንዴ አሕመድ በበኩላቸው ÷ በማህበረሰቡ ዘንድ በባህል፣ ሃይማኖትና በተለያዩ ልማዳዊ አመለካከቶች ምክንያት ከሞት በኋላ አካልን የመለገስ ፍላጎትና ልምድ አነስተኛ መሆኑ ለሕክምናው ተግዳሮት መሆኑን ገልፀዋል።
ይህንን ችግር ለመቅረፍ ማንኛውም ሰው በሕይወት እያለ የዓይን ብሌኑን ለመለገስ ቃል በመግባት ፍቃደኝነቱን ማረጋገጥ እንዳለበት አብራርተዋል፡፡
በተስፋሁን ከበደ

