Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የሠራዊታችንን አኩሪ ተጋድሎ መሰነድና መዘገብ ይገባል – ሜ/ጄ እንዳልካቸው ወልደኪዳን

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 4፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሠራዊታችንን አኩሪ ተጋድሎ መሰነድና መዘገብ ይገባል አሉ የመከላከያ ሚዲያና ኮሙኒኬሽን ማዕከል ኃላፊ ሜጀር ጀኔራል እንዳልካቸው ወልደኪዳን።

ከዕዝና ከተለያዩ ክፍሎች ለተውጣጡ የሚዲያ ሙያተኞች በመከላከያ ሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን ማዕከል አማካኝነት ስልጠና ተሰጥቷል።

በስልጠና ማጠቃለያ መርሐ ግብሩ ላይ ሜጀር ጀኔራል እንዳልካቸው ወልደ ኪዳን ባስተላለፉት መልዕክት፤ ሠራዊቱ ከተጣለበት ሀገራዊ አደራና ከሚፈፅመው ውጤታማ ተልዕኮ አንፃር በሚገባ አልተነገረለትም ብለዋል።

ይህንን አካሄድ ለማስተካከል የሠራዊቱን ልፋትና ድካም የሚረዱ እና የጠላትን ሀሰተኛ ፕሮፖጋንዳ ከንቱ የሚያስቀሩ ጀግና ወታደራዊ ጋዜጠኞችን ማፍራት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።

ሠራዊቱ የሚፈፅመው አኩሪ ተጋድሎ በሚዲያዎች ለህዝብ እንዲደርስ መስራት እንደሚገባ ገልጸዋል።

በተለይም አሁን ላይ የሠራዊቱን ስምና ዝና ለማጥፋት የሚጥሩ ኃይሎችን የሀሰት ፕሮፖጋንዳ ተከታትሎ ማጋለጥ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

ከምድርና ከሰማይ ባለፈ የሚዲያው ግንባር አንዱ የጦርነት ዐውድ በመሆኑ የጠላትን ከንቱ ህልም ማምከን የሚያስችል ስራ መሰራቱን አብራርተዋል።

ሰልጣኞች ያገኙትን አቅም በመጠቀም የሠራዊቱን የዕለት ተዕለት ተልዕኮና እሱን ተከትሎ የሚያስመዘግበውን አኩሪ ተጋድሎ መሰነድና መዘገብ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

መከላከያ ግዙፍ የሚዲያ ኮምፕሌክስ እየገነባ መሆኑን ገልጸው፤ በቀጣይ በስፋት የሚሰራ መሆኑን መጠቆማቸውን የመከላከያ ኦንላይን ሚዲያ ለፋና ዲጂታል የላከው መረጃ ያመላክታል።

Exit mobile version