Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ሞጅታባ ኻሜኒ የአባታቸውን ግድያ ለመበቀል ቃል ገቡ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 4፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢራን አዲሱ የበላይ መሪ አያቶላ ሞጅታባ ኻሜኒ የተገደሉትን አባታቸውን አሊ ኻሜኒን ደም መበቀል የመላው የኢራን ሕዝብ ፍላጎት በመሆኑ የአጸፋው ርምጃ እንደሚወሰድ አስታወቁ።

ሞጅታባ ኻሜኒ የአባታቸው ሥርዓተ ቀብር መፈጸሙን ተከትሎ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ካለአግባብ የንጹሃንን ህይወት የቀጠፉ ወንጀለኛና ክብር የለሽ ነፍሰ ገዳዮችን ለመበቀል ቃል እንገባለን ብለዋል።

ለሳምንት ያህል ሲካሄድ የቆየው የሽኝት ሥነ ስርዓት ተጠናቅቆ የኢራን የቀድሞው መሪ ሥርዓተ ቀብራቸው ተፈጽሟል።

አሜሪካና እስራኤል በኢራን ላይ በሰነዘሩት ጥቃት አሊ ኻሜኒ መገደላቸውን ተከትሎ ኢራን ተከታታይ የአጸፋ ርምጃዎችን መውሰዷ ይታወሳል።

በሌላ በኩል ኢራን የአሜሪካውን ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕን ለመግደል አዲስ እቅድ ማውጣቷን የሚያሳዩ መረጃዎች ደርሶኛል ስትል እስራኤል በቅርቡ ለአሜሪካ የደህንነት መረጃ ማጋራቷን ዘገባዎች አመላክተዋል።

ይህንን ተከትሎ ፕሬዚዳንት ትራምፕ በማህበራዊ ትሰስር ገጻቸው በኩል ኢራን በእሳቸው ላይ የግድያ ሙከራ ካደረገች በሺዎች የሚቆጠሩ ሚሳኤሎችን በኢራን ላይ እንደሚተኩሱ ማስጠንቀቃቸውን የዘገበው አናዶሉ ነው።

ቴህራን እና ዋሽንግተን በሁሉም ግንባሮች ላይ የሚደረጉ ውጊያዎች በአስቸኳይ እንዲቆሙ፣ አሜሪካ በኢራን ላይ የጣለችው የባህር ኃይል እገዳ እንዲነሳ እና የሆርሙዝ ሰርጥ በድጋሚ እንዲከፈት የሚያስችል ስምምነት ተፈራርመው ነበር።

ይሁን እንጂ በሆርሙዝ ሰርጥ በኩል በሚያልፉ የንግድ መርከቦች ላይ ጥቃት በመሰንዘሩ ምክንያት በሁለቱ ወገኖች መካከል ተቀዛቅዞ የነበረው ውጊያ በድጋሜ እየተባባሰ መምጣቱ ይታወቃል።

በቱርክ በተካሄደው የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን (ኔቶ) ስብሰባ ላይ የተገኙት ፕሬዚዳንት ትራምፕ ከኢራን ጋር የተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት ማብቃቱን መግለጻቸው ይታወሳል።

በዮናስ ጌትነት

Exit mobile version