አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 5፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ፊፋ በ2030 የዓለም ዋንጫ ተሳታፊ ሀገራትን ቁጥር ወደ 64 ለማሳደግ እያጤነ መሆኑን ገለጸ፡፡
ከፈረንጆቹ 1998 እስከ 2022 ድረስ የዓለም ዋንጫ በ32 ተሳታፊ ሀገራት ሲካሄድ መቆቱ ይታወሳል፡፡
በአሜሪካ፣ ካናዳ እና ሜክሲኮ ጥምር አስተናጋጅነት እየተካሄደ በሚገኘው በ2026ቱ የዓለም ዋንጫ ውድድር ደግሞ የተሳታፊ ሀገራት ቁጥር ወደ 48 ከፍ ማለቱ ይታወቃል፡፡
የፊፋ ፕሬዚዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ ከአራት ዓመታት በኋላ በሚደረገው የዓለም ዋንጫ የተሳታፊ ሀገራትን ቁጥር ወደ 64 ለማሳደግ በቀረበው አዲስ የውድድር ቅርጽ ላይ ውይይት እንደሚደረግ ጠቁመዋል፡፡
ፖርቹጋል፣ ስፔን እና ሞሮኮ በፈረንጆቹ 2030 የሚካሄደው የዓለም ዋንጫ ውድድር አዘጋጅ ሀገራት ናቸው፡፡
በ2030 የዓለም ዋንጫ ከአዘጋጆቹ ሀገራት በተጨማሪ ኡራጓይ፣ አርጀንቲና እና ፓራጓይ በውድድሩ መጀመሪያ ላይ ጨዋታዎችን እንዲያስተናግዱ ዕቅድ መያዙን አመልክተዋል፡፡
ጂያኒ ኢንፋንቲኖ ከ2026 የዓለም ዋንጫ መጠናቀቅ በኋላ የተሳታፊ ሀገራትን ወደ 64 የማሳደግ ዕቅድ በሚመለከታቸው አካላት ተመክሮበት ይፋ የሚደረግ ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡
ሁሉም ሀገራት በዓለም ዋንጫው የመሳተፍ እድላቸውን ማስፋት እንደሚገባ የገለጹት ፕሬዚዳንቱ፥ ይህም የሀገራቱን የእግር ኳስ ደረጃ ለማሳደግ ይረዳል ማለታቸውን ዘ አትሌቲክ ዘግቧል፡፡

