Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የሁላችንም የጋራ መሻት የሆነውን ሰላምና ልማት ለማስፈጸም በጋራ መስራት አለብን – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 5፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሁላችንም የጋራ መሻት የሆነውን ልማትና ሰላም በጋራ ለማስፈጸም መስራት አለብን አሉ፡፡

የደብረ ማርቆስ ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት አውሮፕላን ማረፊያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት በዛሬው ዕለት በይፋ ተመርቋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፥ ከመወያየትና ከሰላም ውጪ ያለው አማራጭ ለኢትዮጵያ አይጠቅምም ብለዋል፡፡

አማራ እና ኦሮሞ እያለ የሚከፋፈል ማንኛውም ሰው ጎጃም እና ጎንደር፣ ምስራቅ ጎጃም እና ምዕራብ ጎጃም መባባሉ አይቀርም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ አንዴ እየተከፋፈለ የሄደ ማህበረሰብ ማቆሚያ የለውም ሲሉ አስረድተዋል፡፡

የሚሻለውና የሚበጀው የሚያለያየንን ነገር እየተወያየን የሁላችንም የጋራ መሻት የሆነውን ልማት እና ሰላም በጋራ ለማስፈጸም መስራት ነው ብለዋል፡፡

ከዚህ ውጪ ያለው አማራጭ ሀገራችንንና ህዝባችንን ከመጉዳት ባሻገር አንዳች ጥቅም አያስገኝም ነው ያሉት፡፡

ሰላም በእጅጉ አስፈላጊ ስለሆነ መንግሥት ከህዝቡ ጋር በመተባባር ሊወያዩ ለሚፈልጉ ማንኛውም ሰዎች በሩ ክፍት መሆኑን አመልክተዋል፡፡

በመወያየትና በመቀራረብ ሀገራችንን ሰላም እናድርግ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፥ በማያግባቡ ጉዳዮች ላይ በሰላማዊና በሰለጠነ የፖለቲካ አግባብ መነጋገር እንደሚቻል አስረድተዋል፡፡

ውጊያ አዲስ እንዳልሆነና በየዘመናቱ ቀደምት አባቶች እንዳለፉበት ጠቁመው፤ ከኪሳራና ሞት ውጪ ጥቅም አልተገኘበትም ብለዋል፡፡

ስለዚህም አሁን ሊበቃን ይገባል ያንን በጋራ መወሰን አለብን በማለት አሳስበው፤ የምናየውን ትተን የምንሰማውን ብቻ እየወሰድን ብንለያይ ኪሳራው የበዛ ይሆናል ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡

በተደመረ መንፈስ ለልማት መነሳት አስፈላጊ መሆኑን ገልጸው፤ ልማት በባህሪው ጊዜ፣ ትብብር እና ጥበቃ ይፈልጋል ነው ያሉት፡፡

ጊዜ፣ ትብብር እና ትዕግስት ለሚመልሰው ጉዳይ መለያየትና መገዳደል ባህላችን እንዳይሆን መትጋት አለብን ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ጥንታዊት፣ ታሪክ ጠገብ፣ ሰላሙንም ጦርነቱንም የምታቅ ሀገር ነች፤ የጎደላት ልማት እና ብልጽግና መሆኑን አመልክተዋል፡፡

በመደማመጥና በመከባበር በታሪክ ላይ ቆሞ መልካሙን ወስዶ የቀረውን እየሞላ የተሻለች ሀገር ለልጆቻን ማስረከቡ ነው ችግር የነበረው፤ ያንን ችግር ለመፍታት በጋራ መቆም አለብን ሲሉም አሳስበዋል፡፡

በወንድማገኝ ጸጋዬ

Exit mobile version