የኢትዮጵያ አቪዬሽን ዘርፍ በአፍሪካ ቀዳሚ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ በከፍተኛ ፍጥነት በማደግ ላይ ያለ ግዙፍ የኢኮኖሚያዊ ሞተር ሆኗል።
ዘርፉ በሀገሪቱ የቱሪዝም እና የንግድ እንቅስቃሴ ውስጥ ከ2 ቢሊዮን ዶላር በላይ ለሀገር ውስጥ ምርት አስተዋፅኦ እያበረከተ ይገኛል።
አየር መንገዱ በአሁኑ ወቅት ከ165 በላይ እጅግ ዘመናዊና ለአካባቢ ጥበቃ ተስማሚ የሆኑ አውሮፕላኖች አሉት።
አማካይ የእድሜ ዘመናቸውም ከ7 ዓመት በታች ነው።
አየር መንገዱ ተጨማሪ 67 አዳዲስ አውሮፕላኖችንም አዝዟል።
በአፍሪካ ውስጥ ካሉ ማናቸውም አየር መንገዶች በላይ ወደ 131 የሚጠጉ ዓለም አቀፍ መዳረሻዎች፤ 63 የአፍሪካ ከተሞችን ጨምሮ መደበኛ የመንገደኞችና የጭነት በረራዎችን ያደርጋል።
በአቪዬሽን ዘርፉ ባሳየው ተከታታይ ስኬት፣ በ2024/2025 ብቻ 7.6 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ገቢ በማመንጨት 19 ሚሊዮን መንገደኞችን አጓጉዟል።
በዚህ ዓመት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠለት የቢሾፍቱው የአቡ ሴራ ግዙፍ የአውሮፕላን ማረፊያ ከተማ ግንባታ በከፍተኛ ፍጥነት እየተከናወነ ይገኛል።
ፕሮጀክቱ 12.5 ቢሊዮን ዶላር የሚፈጅ ሲሆን፣ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ በዓመት 110 ሚሊዮን መንገደኞችን የማስተናገድ አቅም ይኖረዋል።
ይህም በአፍሪካ ትልቁ ያደርገዋል።
ፕሮጀክቱ የአሁኑን የቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ መጨናነቅ በመቀነስ፣ ኢትዮጵያን እንደ ዱባይና ኢስታንቡል የዓለም አቀፍ ትራንዚት ዋና ማዕከል ያደርጋል።
በአሁኑ ወቅት አየር መንገዱ ራዕይ 2035 ስትራቴጂን ቀርጾ በመተግበር የሀገር ውስጥ የበረራ ተደራሽነቱን ወደ 26 አሳድጓል።
በዚህ ስትራቴጂክ ዕቅድ ከ105 በላይ አዳዲስ አውሮፕላኖችን ከቦይንግ እና ኤርባስ ኩባንያዎች ጋር ውል ፈጽሞ በመጠባበቅ ላይ ይገኛል።
ይህም በሚቀጥሉት ዓመታት ጠቅላላ የአውሮፕላኖቹን ቁጥር ከ270 በላይ ለማድረስ ያለመ ነው።
በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ ሦስት አዳዲስ ዘመናዊ የክልል አውሮፕላን ማረፊያዎች ተገንብተው ሥራ ጀምረዋል።
እነዚህም ነጌሌ ቦረና ገዳ አውሮፕላን ማረፊያ፣ ጎሬ መቱ አውሮፕላን ማረፊያና ዛሬ የተመረቀው የደብረ ማርቆስ ንጉሥ ተክለሃይማኖት አውሮፕላን ማረፊያ ናቸው።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ ትልቁን የጭነት አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን፣ በዓመት ከ248,400 ቶን በላይ ዕቃዎችን ያጓጉዛል።
ይህም የሀገሪቱን የወጪ ንግድ፣ የአበባ፣ ቡና፣ እና አትክልት በቀጥታ ከዓለም ገበያ ጋር በማስተሳሰር የኢኮኖሚ ዋስትና ሆኗል።
እንደ ዓለም አቀፉ የአየር ትራንስፖርት ማኅበር ሪፖርት፣ በኢትዮጵያ ያለው የአየር ጉዞ ፍላጎት በሚቀጥሉት 20 ዓመታት ውስጥ በሦስት እጥፍ ያድጋል ተብሎ ይጠበቃል።
ይህ ዕድገት ከ527,000 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ቀጥተኛና በተዘዋዋሪ የሥራ ዕድል ፈጥሯል።

