የገጠር ኮሪደር ልማት የእያንዳንዱን የአርሶ አደር ቤት እና የአኗኗር ዘዬ በመቀየር በቤተሰብ ደረጃ ሁለንተናዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥ የታለመ ሰው ተኮር ልማት ነው።
በከተሞች የተመዘገበውን አመርቂ የኮሪደር ልማት ውጤት ወደ ገጠሪቱ ኢትዮጵያ በማስፋት፣ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል እና ዘላቂ ማኅበራዊ ሽግግርን ለመፍጠር እንደ ዋና መሣሪያ እየተተገበረ ይገኛል።
የገጠር ኮሪደር ልማት የገጠር መንገዶችን ማሻሻል፣ የኤሌክትሪክ ኃይልና የሳተላይት ዲሽ ግንኙነት፣ የንጹሕ መጠጥ ውኃ አቅርቦት እና ዘመናዊ ትምህርት ቤቶችን በአንድ ላይ ያጠቃልላል።
አርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ ከመደበኛ እርሻው ባለፈ የጓሮውን ቦታ በዶሮ እርባታ፣ በንብ ማር፣ በአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም በወተት ልማት እንዲያበለጽግ ያግዛል።
ኮሪደሩ የዛፍ ተከላን በማጎልበት፣ የተፈጥሮ ሀብትን በመጠበቅ መስቦችን ወደ ሥነ-ምሕዳራዊ ቱሪዝም መዳረሻነት ለመለወጥ ሁነኛ መፍትሄ እየሆነ ነው፡፡
ልማቱ አምራች ቀጣናዎችን በቀጥታ ከግብይትና ማቀነባበሪያ ማዕከላት ጋር በማገናኘት የድኅረ-ምርት ብክነትን በመቀነስ፤ የአርሶ አደሩን ገቢም ያሳድጋል።
አርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ ከእንስሳት ጋር በአንድ ክፍል ውስጥ የሚኖሩበትን ባህላዊ አሠራር በማስቀረት፣ ለእንስሳት የተለየ መጠለያ እና ለቤተሰብ ጽዱ የመኖሪያ አካባቢን በማመቻቸት ዘመናዊ የአኗኗር ፍልስፍናን ይዟል፡፡
እሳቤው ከነተግባሩ ቀላል ወጪ የሚጠይቁና በአካባቢው በሚገኙ ግብዓቶች የሚገነቡ ሞዴል የገጠር መንደሮችን በመገንባት፣ ንጹሕ፣ ውብ እና ጤናማ ሕይወት ለዜጎች ማቅረብን ይደግፋል።
ወጣቱ የተሻለ ኑሮ ፍለጋ ወደ ከተሞች የሚያደርገውን ፍልሰት በመግታትም፣ በሚኖርበት አካባቢ ተረጋግቶ ምርታማ እንዲሆን ያደርጋል።
ሞዴል የገጠር መንደሮች እስካሁን በማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ በደቡብ ኢትዮጵያ እና በአማራ ክልል ተገንብተው ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ ችለዋል፡፡
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የተገነባው የገጠር ኮሪደር ልማት፣ ኮሪደሩ በስፋት የተተገበረበት እና ለሌሎች አካባቢዎች በምሳሌነት የሚጠቀስ ነው።
በዚህም በክልሉ በአራት ዋና ዋና ዞኖች ላይ ሞዴል መንደሮች ተገንብተዋል፡፡ አንደኛው በሃላባ ዞን በወራ ዲጆ ወረዳ፣ ሲንቢጣ ቀበሌ የተገነባው ሲሆን፤ ሁለተኛው በከምባታ ዞን በአዲሎ ወረዳ፣ ሃሚዶ ቀበሌ የተገነባውና የሀምባሪቾ ተራራን ወደ ሥነ-ምሕዳር ቱሪዝም የቀየረውን ሥራ ያካትታል። ሦስተኛው በሀዲያ ዞን በሌሞ ወረዳ፣ ዱባንቾ ቀበሌ ውስጥ የተገነባው ሲሆን፣ አራተኛው በስልጤ ዞን ውልባረግ ወረዳ እና በአካባቢው የተገነቡ የገጠር መንደሮች ናቸው።
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ቤንች ሸኮ ዞን ጉረፈርዳ ወረዳ የተገነባው ሞዴል መንደር ለክልሉ የገጠር ሕይወት መሻሻል ምሳሌ የሚሆን ነው፡፡
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጋሞ ዞን ምዕራብ አባያ ወረዳ የሚገኙ የገጠር ቀበሌዎችን የአኗኗር ዘይቤ ለመቀየር ውብ የገጠር የኮሪደር ልማት ስራዎች ተከናውነዋል።
በተጨማሪም በአማራ ክልል በጎንደር ሳይና ሳብያ ቀበሌ የተገነቡት ሞዴል መንደሮች የገጠሩን ማኅበረሰብ ሕይወት የሚያዘምኑ ሆነዋል፡፡
የገጠር ኮሪደር ልማት የኢትዮጵያን የወደፊት ዕጣ ፈንታ የሚወስን ስትራቴጂ ነው።
ከተማን ማዘመን ብቻውን የተሟላ ብልጽግናን ስለማያመጣ፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የአርሶ አደሮችን ሕይወት በጥራት መቀየር የሀገርን የኢኮኖሚ መዋቅር ከሥር መሠረቱ ያሻሽላል።

