Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ብልፅግና የማረጋገጥ ጥረትን በማጠናከር ሀገራችንን በፅኑ መሠረት ላይ ማቆም አለብን – አቶ ሽመልስ አብዲሳ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 6፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የተጀመረውን ብልፅግና የማረጋገጥ ጥረት በማጠናከር ሀገራችንን በፅኑ መሠረት ላይ ማቆም አለብን አሉ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ሽመልስ አብዲሳ።

የኦሮሚያ ክልል መንግሥት የ2018 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም ግምገማ መድረክ መካሄድ ጀምሯል፡፡

አቶ ሽመልስ አብዲሳ በመድረኩ እንዳሉት፤ 7ኛ ጠቅላላ ምርጫ በድል መጠናቀቁ የህዝቡን ዴሞክራሲ መሻት እና የአመራሩን ቁርጠኝነት ያንጸባርቃል።

በየዘርፉ ያለውም አመራር ባለፉት 5 ዓመታት የከፈለው መስዋዕትነት ለመጪው 5 ዓመታት የብልጽግና መሰረት መጣሉን አስታውሰው፤ ፈተናዎችን በማለፍ የተመዘገበውን ስኬት አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ ገልጸዋል።

ውስንነቶችን በመለየት አቅሞቻችንና ዕቅዶቻችንን በማጣጣም፣ የጋራ አቅሞቻችንን በአግባቡ መተግበር ይገባል በማለት ገልጸው፤ በየዕለቱ ብልፅግናችንን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባራትን መፈፀም አለብን ብለዋል።

የብልፅግና ፓርቲ የኦሮሚያ ክልል ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ኃላፊ ከፍያለው ተፈራ በበኩላቸው፤ ካጋጠሙ ፈተናዎች አንፃር የተመዘገቡ ስኬቶች ሀገሪቱ በብልፅግና ጎዳና ላይ መሆኗን የመላክታሉ ሲሉ ገልጸዋል።

ከጊዜ ወደ ጊዜ የተሻለ ስኬት እየተመዘገበ መሆኑ አንስተው፤ ለአብነትም በ2017 በጀት ዓመት 200 ቢሊየን የነበረው የክልሉ ገቢ በዚህ በጀት ዓመት 335 ቢሊየን ብር መድረሱን አንስተዋል።

በ2017 በጀት ዓመት በክልሉ አጠቃላይ የምርት ገቢ 508 ሚሊየን ኩንታል እንደነበር አስታውሰው፤ ዘንድሮ 511 ሚሊየን ኩንታል ምርት መገኘቱን ጠቁመዋል።

በበጀት ዓመቱ ከ21 ሺህ በላይ ፕሮጀክቶችን በ333 ቢሊየን ብር መስራት ተችሏልም ነው ያሉት።

ውጤት የተመዘገበ ቢሆንም አንዳንድ ውስንነቶች መኖራቸው ጠቅሰው፤ ከተያዘው ዕቅድ አንፃር የተገኙ ስኬቶች ሊገመገሙ የሚገባና የአመራር ከቦታ ቦታ የአፈፃፀም ልዩነት ማሳየትም ሊፈተሽ እንደሚገባ አመልክተዋል።

በታምራት ደለሊ

Exit mobile version