Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ሀገር አቀፍ የጸጥታና ፍትሕ አካላት ጉባኤ መካሄድ ጀመረ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 6፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ሀገር አቀፍ የጸጥታና ፍትሕ አካላት ጉባኤ በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ በዛሬው ዕለት መካሄድ ጀምሯል፡፡

ጉባኤው “ሰብዓዊ መብትና የሰላም ግንባታ” በሚል መሪ ቃል ነው በጅግጅጋ ከተማ እየተካሄደ የሚገኘው፡፡

ለሁለት ቀናት በሚቆየው በዚህ ጉባኤ በመላ ሀገሪቱ በህግ ጥላ ስር የሚገኙ ዜጎችን የሰብዓዊ መብት አያያዝ እንደሚገመግም ነው የተገለጸው፡፡

ጉባኤው በክልሉ ያለውን የሰብዓዊ መብት አያያዝ እንደ ተሞክሮ በመውሰድ በህግ ጥላ ስር የሚገኙ ዜጎችን የሰብዓዊ መብት አያያዝ ለማሻሻል ያለመ መሆኑ ተመላክቷል፡፡

የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሀመድ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣ የክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤዎችን ጨምሮ የክልል የጸጥታና ፍትህ አካላት በጉባኤው ላይ ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ በወቅቱ እንዳሉት፤ ሰላማዊና ፍትሐዊ ማህበረሰብ ለመገንባት በጋራ መስራት ይገባል፡፡

በሀገሪቱ ያለዉ የሰብአዊ መብት አያያዝ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ መሻሻሎች እየታየበት እንደሆነ ገልጸው፤ በተለይ በማረሚያ ቤቶች የነበረዉ የሰብአዊ መብት አያያዝ በእጅጉ ተሻሽሏል ብለዋል።

በማረሚያ ተቋማት የጤና፣ የቀለብ፣ መኝታ፣ የህግ ዋስትና አገልግሎት፣ የግጭት አፈታት እንዲሁም የታራሚዎች አያያዝ ላይ የነበረዉ ቅሬታ እየተፈታ መምጣቱን ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን አዘጋጅነት እየተካሄደ የሚገኘው ጉባኤ ዛሬን ጨምሮ ለሁለት ቀናት የሚቆይ ይሆናል፡፡

በሲሳይ ወርቁ

Exit mobile version