Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የኢትዮጵያና ቤኒን የአጋርነት ጉዞ…

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 6፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ እና ቤኒን በዲፕሎማሲ፣ በንግድ፣ በባህልና ሌሎች ዘርፎች ላይ መሰረቱን ያደረገ የሁለትዮሽ ግንኙነት አላቸው፡፡

ቤኒን በፈረንጆቹ 2005 በአዲስ አበባ ኤምባሲዋን መክፈቷን ተከትሎ የሁለቱ ሀገራት የፖለቲካ እና የዲፕሎማሲ ትስስር ይበልጥ እያደገ መጥቷል፡፡

ኢትዮጵያና ቤኒን በአውሮፓውያኑ 2013 የተፈራረሙት አጠቃላይ የትብብር ማዕቀፍ በሀገራቱ የሁለትዮሽ ግንኙነት ጠንካራ መሰረት ጥሏል፡፡

በይፋዊ የስምምነት ማዕቀፎች እና በአፍሪካ ህብረት በኩል በቅርበት እየሰሩ የሚገኙት ሁለቱ ሀገራት በአቪዬሽን እና በንግድ ዘርፎች በትብብር ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡

በተለይ በአቪዬሽን ዘርፍ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ቤኒኗ ኮቶኑ ከተማ የሚያደርጋቸው መደበኛ በረራዎች ሀገራቱ በቱሪዝም፣ በንግድ እና በሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት እንዲቀራረቡ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡

ከዚህ ቀደም አየር መንገዱ ከቤኒን መንግሥት ጋር በመተባበር ሐጂ አድራጊዎችን ወደ መካ በማጓጓዝ ትልቅ አገልግሎት መስጠቱ ይታወቃል፡፡

በተመሳሳይ የሁለቱ ሀገራት የንግድ ልውውጥ በኤሌክትሪክ ማሽኖች፣ በጨርቃ ጨርቅ እና በግብርና ምርቶች ዙሪያ የተመሰረተ ሲሆን ÷ በቀጣይ የንግድና የኢንቨስትመንት አድማሳቸውን ለማስፋት የሀገራት መንግሥታት ውይይቶችን እያደረጉ ይገኛል፡፡

አሁን ላይ የኢትዮጵያና ቤኒን የሁለትዮሽ ግንኙነት በየጊዜው በሚካሄዱ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ጉብኝቶች ይበልጥ እየተጠናከረ ነው፡፡

ከሁለት ዓመታት በፊት የሁለቱ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በተለያዩ ጉዳዮች ላይ መምከራቸው ይታወሳል፡፡ በዚህ ወቅትም ቤኒን በአፍሪካ ጉዳዮች ላይ ያላት የማይናወጥ ቁርጠኝነት የሚደነቅ መሆኑ ተገልጿል፡፡

በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ከተደረገው ውይይት በኋላ በዛሬው ዕለት ደግሞ የቤኒን ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት ሮሙዋልድ ዋዳግኒ ለሥራ ጉብኝት አዲስ አበባ ገብተዋል፡፡

በቆይታቸውም ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)ጋር የሀገራቱን የሁለትዮሽ ግንኙነት ማጠናከርና በጋራ ጥቅሞች ላይ የላቀ ትብብር ማድረግ በሚያስችሉ ዕድሎች ዙሪያ መክረዋል፡፡

በሚኪያስ አየለ

Exit mobile version