አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 6፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ከመሰረታዊ ፍላጎቶች አንዱ የሆነው መጠለያ በዚህ ወቅት የሰው ልጆች ሁሉ አንገብጋቢ ጥያቄ ነው፡፡
የሰዎች ፍልሰት እና የንግድ እንቅስቃሴ በሚበዛባቸው አካባቢዎች በኪራይ የሚቀርቡ የመኖሪያም ሆነ የንግድ ቤቶች ኪራይ ዋጋ ውድነትና ያልተገባ ጭማሪ የተከራዮች ስጋት ነው፡፡
ፈጣን እድገት ያላቸው ከተሞች የስብት ማዕከል መሆናቸው ለነዋሪዎች ከሚያመጧቸው መልካም እድሎች ባልተናነሰ የተለያዩ ጫናዎችንም ያሳድራሉ።
የተሻሉ የሥራ እድሎችን ፍለጋ ወደ ከተሞች የሚደረገው የሕዝብ ፍሰት ከሚፈጥራቸው ጫናዎች መካከል የመኖሪያ ቤት ፍላጎት አንዱ ነው።
ይህ ፍላጎት ለህገ ወጥ ደላሎች እና ለብልሹ አሰራሮች ተጋላጭ ሲሆን፤ አቅምን ያላገናዘበ የመኖሪያ ቤት ኪራይ ዋጋ በተከራዮች ላይ የሚያሳድረው ጫና ሀገራዊ ልማት ላይ ዘርፈ ብዙ ችግሮችን ያስከትላል፡፡
በኪራይ ዋጋ ጭማሪ ምክንያት መኖሪያ ቤት ለመቀየር በሚደረግ እንቅስቃሴ የሚፈጠረው እንግልት ቀላል የሚባል አይደለም፡፡
ልጆች ትኩረታቸውን ትምህርታቸውን ላይ እንዳያደርጉ፣ ሰራተኞች ተረጋግተው ሥራቸውን እንዳይሰሩ እና ሕሙማን የጤና አገልግሎት ክትትላቸውን እንዲያቋርጡ በማድረግ ዜጎችን ለከፍተኛ ጫና ይዳርጋል፡፡
ለዚህም መንግሥት የቤት አከራይ እና ተከራይ ግንኙነት በህጋዊ መንገድ እንዲመራ ጥረት እያደረገ ይገኛል፡፡ የአከራይ ተከራይ ውል፣ አዋጅና መመሪያዎች የአከራይንና የተከራይን መብትና ግዴታ በሕግ ማዕቀፍ የሚመሩ ናቸው።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በቅርቡ ባወጣው መመሪያ መሰረት የቤት ኪራይ ውሎችን በግልጽ መመዝገብ እና ህጋዊ አሰራርን መከተል ይገኙበታል።
በአዲሱ መመሪያ መሰረት ማንኛውም የአከራይ ተከራይ ስምምነት በጽሑፍ ተዘጋጅቶ፤ በአከራይ፣ በተከራይ እና በሚመለከታቸው አካላት መፈረም አለበት።
የኪራይ ዋጋ ማሻሻያ ጣራ በመመሪያው መሰረት አከራዮች ሊያደርጉ የሚችሉት የቤት ኪራይ ጭማሪ ከፍተኛው ወሰን 11 ነጥብ 5 በመቶ ነው።
ውሃ፣ ስልክ፣ መብራት እና ጥበቃን የመሳሰሉ የአገልግሎት ክፍያ ወጪዎች የአከራይና ተከራይ ስምምነትን መሰረት ያደረጉ መሆን እንደሚገባቸው ተቀምጧል፡፡
በአከራይና ተከራይ መካከል የሚፈጠሩ ጉዳዮች በአዋጁ መሰረት በጽሑፍ ለሚመለከተው ተቆጣጣሪ አካል ቀርበው መፍትሄ የሚያገኙ ይሆናል፡፡
ያለ አግባብ ነባር ተከራዮችን አፈናቅሎ በከፍተኛ ዋጋ ለሌላ ተከራይ ማከራየት የተከለከለና ከህግ አግባብ ውጪ የሆነ አሰራር ነው።
በመሆኑም አዋጁ ተከራዮች ቤት ሲቀይሩ የሚደርስባቸውን ዘርፈ ብዙ እንግልትና ጫና በማስቀረት ማህበራዊ አብሮነትን እንደሚያጠናክር ይታመናል፡፡
በምህረት ደምሴ

