አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 6፣2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአንድ ሀገር ዘላቂ ልማትና ሁለንተናዊ ብልጽግና መሠረቱ ጠንካራና አስተማማኝ የማክሮ ኢኮኖሚ መዋቅር ነው።
ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ያጋጠሟትን ዘርፈ-ብዙ የኤኮኖሚ ፈተናዎች፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረትንና የዕዳ ጫናዎችን በዘላቂነት ለመቅረፍ ሰፊና ታሪካዊ የተባሉ የፖሊሲ ማሻሻያዎችን በመተግበር ላይ ትገኛለች።
በዚህም የኢትዮጵያ ማክሮ ኢኮኖሚ ባለፉት ዓመታት መዋቅራዊ ለውጦችን በማድረግ ላይ ይገኛል።
በተለይም በቅርቡ የተተገበረው የማክሮ ኢኮኖሚ የፖሊሲ ማሻሻያ የውጭ ምንዛሪ ተመን በገበያ እንዲወሰን ማድረጉ፣ የፊስካል ፖሊሲ ማስተካከያዎች እና የውጭ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ የተወሰዱ እርምጃዎች የሀገሪቱን የኢኮኖሚ አቅጣጫ እየቀየሩት ነው።
የመደመር መንግሥት የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ዘላቂና የግል ዘርፉን መሪ ለማድረግ አጠቃላይ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን በመተግበር ላይ ይገኛል። ይህ ሪፎርም በዋናነት የሀገር ውስጥ ምርትን ለማሳደግ፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረትን ለመቅረፍ እና የፊስካል መረጋጋትን ለመፍጠር ያለመ ነው።
በተደረገው የውጭ ምንዛሪ ተመን ማሻሻያ የኢትዮጵያ ብር ከውጭ ምንዛሪዎች ጋር ያለው ተመን በገበያ ፍላጎትና አቅርቦት ላይ ተመስርቶ እንዲወሰን ተደርጓል።
ይህም በሕገ-ወጥ የጥቁር ገበያ እና በሕጋዊው ባንክ መካከል የነበረውን ልዩነት በማጥበብ ረገድ ትልቅ እርምጃ ነው።
የፊስካል እና የገንዘብ ፖሊሲ ማስተካከያ የብሔራዊ ባንክ የገንዘብ አቅርቦትን በመቆጣጠር የዋጋ ንረትን ለመቀነስ እየሰራ ይገኛል።
የመንግሥት በባንኮች ላይ የነበረውን ቀጥተኛ ብድር በመገደብ ረገድም አዳዲስ መመሪያዎች ተተግብረዋል።
ከዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት እና ከዓለም ባንክ ጋር በመተባበር የሀገሪቱን የውጭ ዕዳ ጫና ለመቀነስ የሚያስችሉ የውጭ ዕዳ ሽግሽግ፣ የገንዘብ ድጋፎችና የብድር ማሻሻያ ስምምነቶች ተደርገዋል።
ማሻሻያው የኢኮኖሚ ቁልፍ አንቀሳቃሾች በሚባሉት ግብርና፣ የወጪ ንግድ፣ ኢንዱስትሪ፣ አምራች ዘርፍና የአገልግሎት ዘርፍ ላይ የሀገሪቷን አቅም ማሳደግ ችሏል፡፡
ግብርና አሁንም የኢኮኖሚው መሠረት እንደሆነ ይታወቃል፤ ቡና፣ የቅባት እህሎች እና አበባ ዋና የውጭ ምንዛሪ ግኝት ምንጮች በመሆን፤ እሴት በማከል ላይ መሰራቱ የዘርፉ ላኪነት እንዲጎለብት አግዟል፡፡
የአገልግሎት ዘርፍ እና የኢንዱስትሪውን ሁኔታ ስንመለከት የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የቴሌኮም ዘርፍ (በተለይ የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ መግባትና የኢትዮ ቴሌኮም መስፋፋት) እና የኢንዱስትሪ ፓርኮች ለኢኮኖሚው እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡
የአምራች ዘርፍ የሀገር ውስጥ ምርትን መተካት ላይ ያተኮሩ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄዎችን በማድረግ የሀገር ውስጥ አቅምን ለማሳደግ እየረዱ ይገኛሉ።
በእነዚህ ዘርፎች የተሰሩ ሥራዎችን ስንመለከት የመደመር መንግሥት የጀመረው አጠቃላይ የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም የሀገሪቱን የገበያ ሥርዓት ወደ አዲስ ምዕራፍ እያሸጋገረ እንዳለ እንረዳለን፡፡
በአጠቃላይ፣ የኢትዮጵያ ማክሮ ኢኮኖሚ እድገት አሁን እየተከተለ ያለው የፖሊሲ ማሻሻያ ጎዳና ሀገሪቱን ወደ ተሻለና ወደተረጋጋ የኢኮኖሚ ምህዳር የሚያሸጋግር ትክክለኛ እርምጃ ነው።
በተደረገው ማሻሻያ፣ የፊስካልና የገንዘብ ፖሊሲ የረጅም ጊዜ ጥቅማቸው የላቀ ነው።
የውጭ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ፣ የጥቁር ገበያን ለማስቀረት እና የግል ዘርፉን የኢኮኖሚው መሪ ለማድረግ የተዘረጉት መዋቅሮች ለሀገራዊ እድገት አዲስ ተስፋ የፈነጠቁ ናቸው።
በመሆኑም የተጀመሩትን ማሻሻያዎች በቁርጠኝነት ማስቀጠልና የሚያጋጥሙ የጎንዮሽ ጉዳቶችን በስትራቴጂው ማቃለል ከተቻለ፣ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በምሥራቅ አፍሪካ ብሎም በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪና ጠንካራ መሆኑ የማይቀር ነው።

