አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 6፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ለክረምት ዝናብ መፈጠር ምቹ ሁኔታ የሚፈጥሩ የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች በሚቀጥሉት ቀናት ተጠናክረው ይቀጥላሉ አለ የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ።
ኢንስቲትዩቱ እንደገለጸው ÷ እስከ ሐምሌ 13 ቀን 2018 ዓ.ም የሚኖረው የአየር ሁኔታ ለክረምት ዝናብ ምቹ ሁኔታን የሚፈጥሩ የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች ይበልጥ እየተስፋፉና እየተጠናከሩ የሚሄዱበት ነው፡፡
በዚህም በደቡብ ምዕራብ፣ በምዕራብ፣ በሰሜን ምዕራብ፣ በሰሜን፣ በመካከለኛው እና በምሥራቅ የሀገሪቷ ክፍሎች ላይ የተሻለ የዝናብ መጠንና ሥርጭት እንደሚኖራቸው ይጠበቃል።
በደቡብ ምዕራብ፣ በምዕራብና በሰሜን ምዕራብ የሀገሪቱ አካባቢዎች በአብዛኛው ቦታዎች ላይ ከመካከለኛ እስከ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ ትንበያው አመላክቷል።
እንዲሁም የመካከለኛው፣ የሰሜን ምሥራቅና የምሥራቅ የሀገሪቱ አካባቢዎች ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚኖራቸው አሀዛዊ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ በሆኑ የሀገሪቱ አካባቢዎች በሚቀጥሉት ቀናት አብዛኛውን ቦታዎች የሚሸፍን ከመካከለኛ እስከ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ ይኖራቸዋል፡፡
በደቡብ ምዕራብ፣ በምዕራብ፣ በሰሜን ምዕራብ፣ በሰሜን ምሥራቅና በመካከለኛው የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚኖር ተጠቁሟል።
በሚቀጥሉት ቀናት በደቡብ ምዕራብ፣ በምዕራብና በሰሜን ምዕራብ የሀገሪቱ አካባቢዎች ከመካከለኛ እስከ ከባድ መጠን ያለው እርጥበት እንደሚኖራቸው ተጠቅሷል።
በመካከለኛው፣ በሰሜን ምሥራቅና በምሥራቅ የሀገሪቱ አካባቢዎች ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው የአፈር ውስጥ እርጥበት እንደሚጠበቅም ተገልጿል።
በመሆኑም የሚኖሩ መልካም አጋጣሚዎችን ለመጠቀምና የሚጠበቁ አሉታዊ ተጽዕኖዎችን ለመቀነስ ቦታ ተኮር የግብርና ሚቲዎሮሎጂ ምክረ ሀሳቦችን ከወዲሁ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚያስፈልግ የኢንስቲትዩቱ መረጃ አመልክቷል፡፡

