አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ ሁለት የብድር ስምምነት ረቂቅ አዋጆችን መርምሮ አጽድቋል።
6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 2ኛ አስቸኳይ ስብሰባውን አካሂዷል።
ምክር ቤቱ በኢትዮጵያ እና በጣሊያን ሪፐብሊክ መንግሥት እንዲሁም ከዓለም ባንክ ለ3ኛው ለዘላቂና አስተማማኝ ልማት ለኢትዮጵያ የሚሰጥ የበጀት ድጋፍ ማስፈጸሚያ የሚውል የብድር ስምምነትን በሙሉ ድምፅ ማጽደቁ ተመላክቷል፡፡
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ ቤልጂጌ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት የብድር ስምምነቱ 70 ሚሊዮን ዩሮ ሲሆን ምንም ዓይነት የአገልግሎት ክፍያ እንደማይጠየቅበት ገልጸዋል፡፡
የብድር ስምምነቱ 16 ዓመት የችሮታ ጊዜ ያለው ሲሆን፤ በ30 ዓመት ጊዜ ውስጥ ተከፍሎ የሚጠናቀቅ የረጅም ጊዜ ብድር መሆኑን ጠቁመው፤ብድሩ ቀጥታ ወደ መንግሥት በጀት ፈሰስ እንደሚደረግ አብራርተዋል፡፡
በተጨማሪም ምክር ቤቱ በኢትዮጵያ መንግሥት እና በፈረንሳይ መንግሥት መካከል የትዕዛዝ ቁጥጥርና ንብረት አስተዳደር ሥርዓቶችን የደረጃ አወጣጥ የዲጂታላይዜሽን ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ የሚውል የብድር ስምምነትን መርምሮ በሙሉ ድምፅ አጽድቋል።
በምክር ቤቱ የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ስምምነቱን አስመልክቶ እንዳሉት፤ ስምምነቱ 54 ሚሊየን 600 ሺህ ዩሮ የፋይናንስ ድጋፍ የያዘ መሆኑን ገልጸዋል።
የብድር ስምምነቱ በ10 ዓመት የችሮታ ጊዜ ውስጥ በ25 ዓመት ተከፍሎ የሚጠናቀቅ መሆኑን ጠቅሰው፥ የወለድ መጠኑም 0 ነጥብ 347 በመቶ ዝቅተኛ መጠን ያለው መሆኑን አስረድተዋል፡፡

