Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የካፒታል ገበያ ለሀገር ኢኮኖሚ …

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በምንኖርበት መንደር ካለ አነስተኛ ጉልትና ሸቀጣሸቀጥ ሱቅ ጀምሮ እስከ ትላልቅ ሱፐር-ማርኬቶችና የንግድ ማዕከላት ከዚያም ሲያልፍ ዓለም አቀፍ የንግድ ልውውጦች የሚካሄድባቸው መድረኮች በጠቅላላ ገበያ በመባል ይታወቃሉ፡፡

በእነዚህ ገበያዎች ሻጮች ለያዙት ቁስ ወይም አገልግሎት ያዋጣኛል የሚሉትን ዋጋ ይለጥፉበታል፤ ገዢም በፊናው አቅሜ ይፈቅድልኛል ባለው ስፍራና ዋጋ ይሸምታል፡፡

በዋጋ ላይ የሚደረግ ድርድርም ከትንሹ ጉልት እስከ ሀገር አቀፍና ዓለም አቀፋዊ ገበያዎች ላይ የተለመደ ነው፡፡ ነገር ግን የገበያው ዓለም እኛ በዕለት ከዕለት ህይወታችን ከምናውቀው አይነት የተለዩ አካሄዶችን በውስጡ አካትቷል፡፡

የፋይናንሺያል (የሒሳብ) ገበያ የምንለው ተለያዩ የሒሳብ ሰነዶችን የምንገበያይበት መድረክ ነው፡፡ ለምሳሌ እንደ አክሲዮንና ቦንድ የመሳሰሉት ሰነዶች ለገበያ የሚቀርቡበት ነው፡፡

የፋይናንሺያል (የሒሳብ) ገበያን የገንዘብ ገበያና የካፒታል ገበያ በሚል በሁለት ከፍለን እናየዋለን። የገንዘብ ገበያ ለአጭር ጊዜ የሚቆዩ የፋይናንስ ሰነዶችን የምንገበያይበት ሲሆን የካፒታል ገበያ ደግሞ ማንኛውንም ገንዘብን የያዘ የረጅም ጊዜ የሒሳብ ሰነድን የምንገበያይበት ቦታ ነው፡፡

ዋና ዓላማውም ሰነዶቹን በመውሰድ ገዢዎችና ሻጭን እንዲገበያዩዋቸው መድረኩን ማመቻቸት ነው፡፡

የካፒታል ገበያዎች ዓላማ ለሽያጭ የሚቀርብ አክሲዮን ያላቸውን ድርጅቶችንና ገንዘብ ያላቸውን ገዢዎች በማገናኘት የሽያጭ ሂደቱን ማሳለጥ ነው፡፡

ይህ ገበያ ካፒታልን በማከፋፈል የፋይናንስ እጥረት እንዳያጋጥም ይረዳል፤ በተጨማሪም የንግድ ድርጅቶች አቅማቸውን እንዲያሳድጉ በማድረግ አዳዲስ ፕሮጀክቶች ላይ መዋዕለ ነዋያቸውን እንዲያፈሱ አስተዋጽኦ በማድረግ የስራ ዕድል በመፍጠር ትልቅ ትርጉም አለው፡፡

ካፒታል ገበያ ለኩባንያዎች ለምርምር እና ለማስፋፊያ ልማት ስራዎች ገንዘብ ለማሰባሰብ መድረክ ስለሚሰጣቸው ፈጠራን፣ የቴክኖሎጂ ሽግግርን እና ቀጣይነት ያለው እድገትን የሚያስመዘግቡ ኢንዱስትሪዎችን ለመመስረት ያግዛል።

በተጨማሪም ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል እንዲኖር የሚያደርግ በመሆኑ ዜጎች መዋዕለ ነዋያቸውን እንዲያፈሱና እና ከኢንቨስትመንቱም ትርፍ እንዲያገኙ ያስችላቸዋል።

ካፒታል ገበያ ውጤታማ የካፒታል ገበያ መዋዕለ ነዋያቸውን ማፍሰስ የሚፈልጉ የውጭ ኢንቨስተሮችን በመሳብ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ያሳድጋል።

በርካታ ትሩፋቶች ያሉት የካፒታል ገበያ፤ በኢትዮጵያ ያለውን ታሪካዊ ዳራ ስንመለከት በ1889 ዓ.ም የኢትዮ- ጂቡቲን የምድር ባቡር ፕሮጀክትን ለመስራት በፈረንሳይ ሀገር የ40 ሚሊየን ፍራንክ አክሲዮን ለገበያ መቅረቡን ታሪክ ያወሳል፡፡

በ1948 ዓ.ም ኢትዮጵያ የካፒታል ገበያን ለማቋቋም ሙከራ አድርጋ ነበር፤ በዚህም የኢትዮጵያ ቄራዎች ድርጅት የመጀመሪያውን አክሲዮን ሽያጭ አቅርቦ እንደነበር ይነገራል፤ ይህም በሀገሪቱ የፋይናንስ ታሪክ ውስጥ ትልቅ እርምጃ እንደነበር የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ።

በ1957 ዓ.ም የአዲስ አበባ የአክሲዮን ንግድ ማህበር የተቋቋመ ሲሆን ይህ ማህበር ብሔራዊ ባንክን እና ሌሎች ባለሀብቶችን በማካተት የዋስትና ገበያን ለመቆጣጠር ዓላማ አድርጎ ነበር።

ምንም እንኳን ከላይ ያነሳናቸው ጥረቶች ቢኖሩም ጠንካራ የሕግ ማዕቀፎች እና የቁጥጥር ስርዓት ባለመኖሩ ለውጤት ሳይደርስ ቀርቷል።

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የፋይናንስ ሥርዓት ውስጥ ስር ነቀል የሚባል ለውጥ ለማምጣት የተተገበረው የፋይናንስ ሪፎርም፤ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ የሚደግፍ ዘመናዊ የካፒታል ገበያ እንዲቋቋምና እንዲዳብር የሚያስችሉ መሠረታዊ አሰራሮችን በመያዝ የካፒታል ገበያ ተቋቁሞ በርካታ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል።

በዚህም የካፒታል ፍሰትን በማሳለጥ፣ የቁጠባና የኢንቨስትመንት ባህልን በማሳደግ፣ እንዲሁም ቀልጣፋና ፍትሀዊ የገበያ ሥርዓት በመፍጠር ሀገርን በኢኮኖሚ አጠናክሮ ለታለመው ሁለንተናዊ ብልጽግና ለማድረስ ዋነኛ መሰላል በመሆን ሚናውን እየተወጣ ይገኛል፡፡

የካፒታል ገበያ በኢትዮጵያ ውስጥ ትግበራውን ካደረገ ውስን ጊዜያት ብቻ ቢቆጠሩም እያሳየው ያለው መነቃቃትና እያስገኘው ያለው ጥቅም በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡

በመልካም ፈቃዱ

Exit mobile version