አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 7፣2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ በዘንድሮ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት 20 ሚሊየን ዜጎች የጤና አገልግሎት ተጠቃሚ ይሆናሉ አሉ።
የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ህክምና ኮሌጅ የ2018 የክረምት በጎ ፈቃድ ነጻ ምርመራ አገልግሎት በይፋ ጀምሯል።
በማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ ላይ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ሎሚ በዶ፤ የክረምት ወራት በሀገራችን የምንረዳዳበት እና የምንደጋገፍበት ወቅት ነው ብለዋል።
በበጎ ፈቃድ አገልግሎት በመሳተፍ ላይ የሚገኙ ባለሙያዎችን አመስግነው፤ ሀገር ያላትን ውስን ሀብት በመጠቀም የተጀመረውን ልማት ማጠናከር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት የተጀመረው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለሌሎች ሀገራት ተምሳሌት እንደሚሆን የገለጹት የጤና ሚኒስትሯ በበኩላቸው፤ የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን በጤና ስርዓት ውስጥ በማካተት እየተሰራ ነው ብለዋል።
ባለፈው ዓመት ብቻ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት አማካኝነት ለ15 ሚሊየን ዜጎች ነፃ የህክምና አገልግሎት ማቅረብ መቻሉን አስታውሰው፤ በዘንድሮ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት 20 ሚሊየን ዜጎችን የጤና አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ መታቀዱን ገልጸዋል።
በክረምት ወራት በጎ ፈቃድ ብቻ ባለፈው ክረምት 176 ሺህ ዩኒት ደም መሰብሰቡን እና የህክምና መሳሪያዎች ጥገና በማካሄድ ሃብትን ከብክነት ማትረፍ መቻሉን ማስታወሳቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ አመልክቷል።

