አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያውያን በሰለጠነ መንገድ ለመምከር መሰባሰባቸው የኢትዮጵያን ከፍታ ያሳየ ነው አሉ የሰላም ሚኒስትር መሀመድ እድሪስ፡፡
ሚኒስትሩ በነገው ዕለት የሚጀምረውን የምክክር ጉባኤ አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት፥ ኢትዮጵያ የስልጣኔ አብነት፣ የአብሮነት ምልክት፣ የነፃነት ፋና፣ የጥበብ ጀማሪና ባለብዙ ፀጋ መሆኗን አውስተዋል፡፡
እንደ ሀገር የመመካከር ዕድልን በአግባቡ ተጠቅሞ ለልዩነቶች በምክክር መፍትሄ በመስጠት ታሪክ ሰርቶ ማለፍ የዚህ ትውልድ ትልቅ እና አይረሴ ድል ነው ብለዋል፡፡
በታሪክ አጋጣሚ የተፈጠሩና ለአብሮነት እንዲሁም ለዘላቂ ሰላም እንቅፋት የሆኑ ጉዳዮችን ለይቶ ለመፍታት ትኩረት መሰጠቱ መፍትሄ ለማምጣት ትልቅ ሚና ይጫወታል ነው ያሉት፡፡
ኢትዮጵያውያን ስለ ሀገራቸው በሰለጠነ ንግግርና በሰላማዊ ውይይት ለመምከር መሰባሰባቸው የኢትዮጵያን ልጆች ብስለት፣ አርቆ አሳቢነት እንዲሁም የኢትዮጵያን ከፍታና የወደፊት ብሩህ ተስፋ ያሳየ ነው ሲሉም አብራርተዋል።
የሀገራዊ ምክክር ጉባኤው ከነገ ጀምሮ በአዲስ አበባ የሚካሄድ ሲሆን፥ ከ4 ሺህ በላይ የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን እንደሚሳተፉ ተገልጿል፡፡

