Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ሀገራዊ መግባባት ብሔራዊ ጥቅሞችን በዘላቂነት ለማረጋገጥ ቁልፍ ሚና ይጫወታል

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም መርሆዎች የሀገሪቱን ሉዓላዊነት፣ የሕዝብ ደኅንነትና ሰላም፣ ምጣኔ-ሐብታዊ እድገትና ብልጽግና በሚያረጋግጡ መሰረቶች የተገነቡ ናቸው፡፡

በዓለም ላይ የሚገኙ ሀገራት ሉዓላዊነታቸውን አስከብረው በተሻለ ቁመና ለመቀጠል ብሔራዊ ጥቅምን ቀይ መስመራቸው የሚያደርጉ ሲሆን፤ ይህን ጥቅም ለማስከበር ፖሊሲዎች እና ስትራቴጂዎችን ይነድፋሉ፡፡

ይህ ብሔራዊ ጥቅም ታዲያ ከውስጥም ሆነ ከውጭ የሚሰነዘሩ ጣልቃ ገብነቶችን ለመመከት፣ በምጣኔ ሐብት ተወዳዳሪ ለመሆን፣ ከሌላው ሀገር ጋር ግንኙነት ለመፍጠር እና ለማጠናከር ትልቅ ኃይል በመሆን ያገለግላል፡፡

ሀገር ማለት በአንድነት ተባብሮ የሚኖር ሕዝብ፣ የተከለለ ድንበር ያለው፣ የጠንካራ እና ቅቡልነት ያለው የመንግሥት ባለቤት እና  በሉዓላዊነቱ ተከብሮ የሚኖር ሕዝብ ማለት ሲሆን ሀገር የምትቀጥለው ብሔራዊ ጥቅሞቿን አውቃ፣ ቆጥራ እና አስከብራ ስትኖር ብቻ ነው።

ከዚህ አንፃር የመደመር መንግሥት ተለዋዋጩን የዓለም ስርዓት እና የዓለም አቀፍ ግንኙነት ታሳቢ በማድረግ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም መርሆችን፣ ግብ፣ ፍላጎት እና ትኩረቶችን ይፋ አድርጎ ለጥቅሞቹ መከበር እየሰራ ይገኛል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም መርሆዎች የሀገሪቱን ሉዓላዊነት፣ የሕዝብ ደኅንነትና ሰላም፣ ምጣኔ-ሐብታዊ እድገትና ብልጽግና እንዲሁም ራስን መቻልን የሚያረጋግጡ፣ ከትውልድ ትውልድ የሚሸጋገሩ መሠረታዊ የሀገርና የሕዝብ አጀንዳዎች ናቸው።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም መርሆች በአራት ዋና ዋና መርሆች ይጠቃለላሉ።

ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት፦ ይህ የብሔራዊ ጥቅም እሳቤ የሀገሪቱን ነፃነት፣ የድንበር ደህንነት እና ሉዓላዊነትን ማስከበር እንዲሁም ከውስጥም ሆነ ከውጭ የሚሰነዘሩ ጣልቃ ገብነቶችን ለመመከት የሚያስችል እሳቤ ነው፡፡

የሕዝቦች ደኅንነት እና አንድነት፦ የዜጎችን ህይወት፣ ሰላምና ደህንነት መጠበቅ፤ ለፖለቲካ እና አስተዳደራዊ ልዩነቶች ቅድሚያ ሳይሰጡ በሀገር ህልውና ላይ በአንድነት ለመቆም የተቀረፀ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም መርህ ነው፡፡

ምጣኔ-ሐብታዊ ብልጽግና እና ልማት፦ ይህ መርህ ሀገሪቱ ያላትን ጂኦ-ስትራቴጂካዊ አቅም ተጠቅማ ኢኮኖሚያዊ ተወዳዳሪነቷን ማሳደግ፣ ከድህነት መውጣት እና ራስን ለመቻል ያለመ ነው፡፡

የጋራ ተጠቃሚነት እና ተጽዕኖ ፈጣሪነት፦ በዓለም አቀፍና አህጉራዊ መድረኮች የኢትዮጵያን ጥቅም ማስጠበቅ፣ በጎረቤት ሀገራትና በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና መረጋጋትን በማረጋገጥ አወንታዊ ሚና መጫወት የሚያስችል የብሔራዊ ጥቅማችን መርህ ነው፡፡

ከነዚህ መርሆች በተጨማሪ የባህር በር ጥያቄው የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር አንደኛው አጀንዳ ሆኖ ከተነሳ የቆየ ሲሆን ጥያቄው በተለያዩ ሀገራት እና ባለ ብዙ ወገን ተቋማት ዘንድ እውቅናን እያገኘ ይገኛል፡፡

ኢትዮጵያ የምትከተላቸው እነዚህ የብሔራዊ ጥቅም እሳቤዎች በፖለቲካ፣ በአስተሳሰብ፣ በአይዲዮሎጂ እና በመንግስት ስርዓት ታፍራ እና ተከብራ እንድትኖር የሚያስችሉ መሰረቶች ናቸው፡፡

ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ያልተገራ ፍላጎት፣ የውስጥ ባንዳዎች፣ የኢትዮጵያ ጂኦ ስትራቴጂካዊ ተፈላጊነት፣ የሀገረ መንግሥት ግንባታ አለመጠናቀቅ፣ ድህነት እና ኋላቀርነት እና የመልካም አሥተዳደር ችግሮችን ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ፈተናዎች መሆናቸው ይጠቀሳል፡፡

እነዚህን ብሔራዊ ጥቅሞች በዘላቂነት ለማስጠበቅ ውስጣዊ አንድነትን ማጽናት፣ ሰላም እና ደህንነትን ማረጋገጥ፣ የፖለቲካ ባሕልን ማዘመን፣ የሃሳብ ፖለቲካን ማስፈን፣ ከፖለቲካ ኃይሎች ጋር ሰላማዊ አማራጭ መከተል፣ ሀገራዊ መግባባትን መፍጠር፣ የጋራ ትርክትን በጋራ ጥቅም ላይ መገንባት አስፈላጊ ነው፡፡

በሚኪያስ አየለ

Exit mobile version