Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ምክክሩ ለሌሎችም ሀገራት ምሳሌ የሚሆን ነው – አምባሳደር ባንኮሌ አዶዬ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 8፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ለሌሎችም የአፍሪካ ሀገራት ምሳሌ የሚሆን ነው አሉ በአፍሪካ ህብረት የፖለቲካ ጉዳዮች፣ የሰላምና ደህንነት ኮሚሽነር አምባሳደር ባንኮሌ አዶዬ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር በዛሬው ዕለት በይፋ መካሄድ ጀምሯል።

አምባሳደር ባንኮሌ አዶዬ በመርሐ ግብሩ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ ይህ ሀገራዊ ምክክር ለኢትዮጵያ የዴሞከራሲ ግንባታ ሂደት እና ዘላቂ ሰላም ጥረት ትልቅ ማረጋገጫ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ምክከሩ የሀገራዊ ኃላፊነት መገለጫ መሆኑን ጠቅሰው÷ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ እና በፖለቲካ ምህዳሩ ውስጥ መተማመንን ለመፍጠር ያግዛል ብለዋል፡፡

ሀገር በቀል የምክክር ሂደቶች ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአህገሪቱ ምሳሌ እንደሚሆኑ በመገለጽ፤ መሰል ምክክሮች በሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም ሊለመዱ ይገባል ነው ያሉት፡፡

ከህብረቱ አጀንዳ 2063 ዕቅዶች አንዱ በአህጉሪቷ ሰላም ማረጋገጥ እንደሆነ አስታውሰው፤ የአፍሪካ ህብረት ይህንን ታሪካዊ የምክክር ክስተት ሙሉ በሙሉ ይደግፋል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ እና የፓን አፍሪካኒዝም መሪ ሀገር ሆና መቆየቷን ያወሱት አምባሳደር ባንኮሌ፤ የኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም የሁሉም አፍሪካውያን ሰላም መሆኑን አብራርተዋል፡፡

በመድረኩ አምባሳደር ባንኮሌ የብልፅግና ፓርቲ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በማሸነፉ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ለብልጽግና ፓርቲ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክትም አስተላልፈዋል፡፡

በሚኪያስ አየለ

Exit mobile version