Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ኢትዮጵያ የኮፕ32 ሂደትን ለመተግበር ቁርጠኛ ናት – ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 8፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና የኮፕ32 ፕሬዚዳንት ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ጉባዔ (ኮፕ32) ሂደትን ለመተግበር ቁርጠኛ ናት አሉ።
ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) የኮፕ21 ፕሬዚዳንት ከሆኑት ሎረን ፋቢየስ ጋር ስኬታማ የኮፕ32 ጉባኤን ለማካሄድ አስተዋጽኦ ሊኖራቸው በሚችሉ ጉዳዮችና ካለፉት የኮፕ ጉባኤዎች በተገኙ ትምህርቶች እና ግንዛቤዎች ላይ በዛሬው ዕለት ተወያይተዋል።
‎በውይይቱም ሎረን ፋቢየስ በዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ላይ ታላቅ ስኬት የተመዘገበበትን የፓሪስ ስምምነት በማጽደቅ የተጠናቀቀውን ኮፕ21ን የመሩበትን ልምድ አካፍለዋል። ‎
‎ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) የፓሪሱ ስምምነት ለዓለም አቀፍ የአየር ንብረት እርምጃዎች ዘላቂ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸው፤ የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትላቸውን አሉታዊ ተፅዕኖዎች ለመቋቋም የተገቡ ቃሎችን ወደ ተጨባጭ ተግባር የመቀየርን አስፈላጊነት አፅንዖት ሰጥተዋል።
በተጨማሪም ኢትዮጵያ በባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ ላይ እምነትን የሚያጠናክር፣ ግልጽ፣ አካታች እና በአባል ሀገራት የሚመራ የኮፕ32 ሂደትን ለመተግበር ያላትን ቁርጠኝነት በድጋሚ አረጋግጠዋል።
ይዘትና ድርድር፣ ሎጂስቲክስና ኦፕሬሽን፣ አጋርነት እንዲሁም ሚዲያና ኮሙኒኬሽን ጨምሮ በተለያዩ ዘርፎች የሚደረገው ዝግጅት ተጨባጭ ዕድገት ማሳየቱን ተናግረዋል።
Exit mobile version