Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በትግራይ ክልል ያለውን አፈና የሚቃወም ሰላማዊ ሰልፍ የፊታችን ቅዳሜ ይካሄዳል

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 9፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ሕገ ወጡ የሕወሓት ቡድን በትግራይ ክልል ሕዝብ ላይ እያካሄደ ያለውን አፈና የሚቃወም ሰላማዊ ሰልፍ የፊታችን ቅዳሜ በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ ይካሄዳል፡፡

የሰላማዊ ሰልፉ አዘጋጅ የትግራይ ሰላምና ለውጥ ምክር ቤት የሚዲያ ዘርፍ አስተባባሪ አቶ ከበደ አሰፋ ጉዳዩን አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

አቶ ከበደ በመግለጫቸው ሕገ ወጡ የሕወሓት ቡድን በትግራይ ክልል ሕዝብ ላይ ዘርፈ ብዙ አፈና እና ስቃይ እያደረሰ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

የፊታችን ቅዳሜ ሐምሌ 11 ቀን 2018 ዓ.ም ከጠዋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ በትግራይ ክልል ያለውን አፈና የሚቃወም ሰላማዊ ሰልፍ በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ እንደሚካሄድ አመልክተዋል፡፡

ሰልፉ የትግራይ ሕዝብ እየተካሄደበት ያለውን አፈና እና ሰቆቃ ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ እንዲሁም የፌዴራል መንግሥት እንዲያውቁና ርምጃ እንዲወሰዱ ለማድረግ ያለመ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡

መላው ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ የፊታችን ቅዳሜ በሚካሄደው ሰላማዊ ሰልፍ በመሳተፍ ድምጹን እንዲያሰማም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በአመለወርቅ ደምሰው

Exit mobile version